Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ምሽ ሲካሄዱ አንጎላ ከናሚቢያ እንዲሁም ናይጀሪያ ከካሜሩን ይጫዎታሉ፡፡

አንጎላ ከናሚቢያ የሚያደርጉት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ምሽት 2 ሰዓት ላይ በቡዋኬ ሰታዴ ዴ ላ ፔይክስ ስታዲየም የሚደረግ ሲሆን በጨዋታው አንጎላ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷታል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ካደረጉት 12 የእርስ በእርስ ግንኙነት ውስጥ አንጎላ በስድስቱ ስታሸንፍ በስድስቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

ሌላኛው በጥሎ ማለፉ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የናይጀሪያ እና የካሜሩን ጨዋታ ምሽት 5 ሰዓት በአቢጃን ስታድ ፊሊክስ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው 25 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ናይጀሪያ 12 ጨዋታዎች፣ ካሜሩን ደግሞ አምስቱን ስታሸንፍ በስምንት ጨዋታዎች አቻ ተለይይተዋል፡፡

በምሽቱ ጨዋታ የናይጀሪያው አሰልጣኝ ጆዜ ፔዜሮ ከምድብ ስኬታማ የሆኑበትን 3-4-3 አሰላለፍ ይዘው እንደሚገቡ የተገለፀ ሲሆን በቡድኑ ጉዳት ያጋጠመው ተጫዋች እንደሌለ ተሰምቷል።

በአንፃሩ ወሳኝ አጥቂውን ቪንሴንት አቡበከር ግልጋሎት ያጣው የካሜሩን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹን በምሽቱ ጨዋታ ለማሰለፍ ጥረት እያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ካሜሩን ከጋምቢያ ጋር በነበራት ጨዋታ ያልተሰለፈው አንድሬ ኦናና ከቀድሞው የቡድኑ ኮከብ ሳሙኤል ኤቶ ጋር ከፈጠረው ውዝግብ በኋላ በዛሬ ምሽቱ ጨዋታ ሊሰለፍ እንደሚችል ካፍ ኦንላይን ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.