Fana: At a Speed of Life!

የሴቶች የስትሮክ ተጋላጭነት

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ስትሮክ በተለያዩ ምክንያቶች በአንጎል ዉስጥ የደም ፍሰት ችግር ሲያጋጥምና የአንጎል ክፍል ሲጎዳ የሚፈጠር የጤና እክል ነው፡፡

ክስተቱ ወደ አንጎል የሚሄደዉ የደም ቧንቧ በመዘጋቱ ምክንያት የአንጎል ክፍል ረዘም ላለ ጊዜ ያለ ደም ሲቆይ(Ischemic stroke) እና የደም ቧንቧ ወደ አንጎል እና ወደ አካባቢው ደም ማፍሰስ ሲጀምር (Hemorrhagic stroke) የሚፈጠር እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ስትሮክ በማንም ሰው ላይ ሊከሰት የሚችል የጤና እክል ቢሆንም በአብዛኛው በእድሜ በገፉና በሴቶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ የአለምአቀፉ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ጥናት ያሳያል፡፡

ማዕከሉ በአሜሪካ ከዚሁ የጤና ችግር ጋር በተያያዘ ባጠናው ጥናት መሰረት በአማካይ ከ5 ሴቶች ውስጥ አንዷ በስትሮክ የመጠቃት እድል እንዳላት የገለጸ ሲሆን÷ ከእነዚህም ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ለህልፈተ ህይዎት እንደሚጋለጡ አመላክቷል፡፡

ሴቶች ከወንዶች በበለጠ ለስትሮክ ተጋላጭ ከሆኑባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል በወሊድ መቆጣጠሪያዎች እና ከእርግዝና ጋር እንዲሁም ከማይግሪን ህመም ጋር የተያይዘ እንደሆነም ነው በጥናቱ የተገለጸው፡፡

በተጨማሪም ÷ ሴቶች ከወንዶች በተፈጥሮ ረዥም እድሜ የመኖር እድል ስላላቸውና በእድሜ ገፋ ያሉ ሰዎች ደግሞ በስትሮክ የመጠቃት እድላቸው ሰፊ ስለሆነ እንደሆነም ጥናቱ ያትታል፡፡

በግልጽ ከሚታወቁት የስትሮክ ምልክቶች ውስጥም የፊት መውደቅ፣ የክንድ ድክመት፣ የንግግር ችግር፣ የአንድ ወይም የሁለቱም ዓይኖች የማየት ችግር፣ ሚዛንን አለመጠበቅ እና ከባድ ራስ ምታት በተለይ÷ በአንዳንድ ሴቶች ላይ እንደ ድካም፣ ማቅለሽለሽ፣ የሰውነት መዛል፣ ማስታወክ ወይም የማስታወስ ችግር ያሉ ስውር የማስጠንቀቂያ ምልክቶች ሊስተዋሉ እንደሚችሉም ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡

ሲጋራ ማጨስ፣ የደም ግፊትና የኮሌስትሮል መጠን መጨመር በሴቶችና ወንዶች ላይ የስትሮክ መንስኤ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

ሴቶች በተፈጥሮ ምክንያት ለስትሮክ የሚጋለጡበትን ሁኔታ ለመቀነስ ከታች የተዘረዘሩትን ጉዳዮች በሕክምና ባለሙያ ድጋፍ ማከናወን እንደሚገባ የኸልዝ ላይን መረጃ አመላክቷል፡፡

እነሱም ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የደም ግፊት ያለባቸው ሴቶች ለስትሮክና ደም ግፊት የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ስለሆነ ፤ ከእርግዝና በፊት ከፍተኛ የደም ግፊት ታሪክ ያላቸው ሴቶች ዝቅተኛ መጠን ያለው የካልሽየም ማሟያ በመውሰድ ከእርግዝና ጋር የተያያዘ የደም ግፊት ስጋትን መቀነስ እንዳለባቸው በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

መካከለኛ የደም ግፊት (150 -159 / 100 – 109) ያለባቸው ነፍሰጡር ሴቶች የደም ግፊት መድሃኒት መውሰድ እንዳለባቸው ለመውለድ የተቃረቡ ከፍተኛ የደም ግፊት (ከ160/110 በላይ) ያለባቸውም የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ ጥናቱ ምክረ ሃሳብ ያቀርባል፡፡

የስትሮክ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የወሊድ መከላከያ እንክብሎችን ከመውሰድ በፊት የደም ግፊትን መመርመር፤የማይግሬንና ራስ ምታት ያለባቸው ሴቶች ከፍተኛ የሆነ የስትሮክ ስጋትን ለማስወገድ ሲጋራ ማጨስ እንዲያቆሙ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.