በመዲናዋ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከልን ለማስፋፋት ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ጥር 27፣ 2016 (ኤፍቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች የሚቀርበውን የምገባ አገልግሎት ለማስፋፋት ባለሃብቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ የከተማ አስተዳደሩ ምገባ ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሽታዬ መሃመድ እንደገለጹት÷ በአዲስ አበባ ከፍተኛ ድጋፍ የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለመርዳት የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
ለአብነትም በመዲናዋ በዝቅተኛ ኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ነዋሪዎች በተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል በቀን አንዴ የምገባ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ በአዲስ አበባ 35 ሺህ የሚሆኑ ዜጎች የምገባ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሯ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ 20 የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከላት መኖራቸውን ጠቁመው÷ በቀጣይ አገልግሎቱን ይበልጥ ለማስፋት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ባለሃብቶች እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቅርበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ