Fana: At a Speed of Life!

በቶሩን የቤት ውስጥ ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸነፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በፖላንድ ቶሩን የቤት ውስጥ ሩጫ ውድድር በተለያዩ ርቀቶች ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፈዋል።

በ1 ሺህ 500 ሜትር የሴቶች የቤት ውስጥ ሩጫ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ በመውጣት ታሪክ ሰርተዋል፡፡

በዚህም ፍሬወይኒ ሃይሉ በ1 ሺህ 500 ሜትር ሴቶች የቤት ውስጥ ሩጫ ታሪክ በርቀቱ ሦስተኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ በቀዳሚነት አጠናቅቃለች፡፡

አትሌቷ የገባችበት 3 ደቂቃ 55 ሰከንድ ከ28 ማይክሮ ሰከንድ የዓመቱ ቀዳሚ ሰዓት ሆኖ መመዝገቡም ተመላክቷል፡፡

በዚሁ ርቀት ድርቤ ወልተጂ 2ኛ፣ ሒሩት መሸሻ 3ኛ እንዲሁም ትዕግስት ግርማ 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቅቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በወንዶች 1 ሺህ 500 ሜትር ውድድር ሳሙኤል ተፈራ ርቀቱን 3 ደቂቃ 34 ሰከንድ ከ61 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በማጠናቀቅ አሸንፏል።

ቢኒያም መሐሪ ደግሞ ከ18 እና ከ20 ዓመት በታች በተደረገ የ1 ሺህ 500 ሜትር ሩጫ ርቀቱን 3 ደቂቃ 34 ሰከንድ ከ83 ማይክሮ ሰከንድ በበማጠናቀቅ የዓለም ክብረ ወሰን መስበር ችሏል፡፡

በወንዶች 3 ሺህ ሜትር ሰለሞን ባረጋ 7 ደቂቃ 25 ሰከንድ ከ82ማይክሮ ሰከንድ በመግባት 5ኛውን ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ ሲያጠናቅቅ ÷ ጌትነት ዋለ እና ግርማ አዲሱ ደግሞ በቅደም ተከትል 2ኛ እና 4ኛ ወጥተዋል።

በሴቶች የ800 ሜትር ሃብታም ዓለሙ 1 ደቂቃ ከ57 ሰከንድ ከ86 ማይክሮ ሰከንድ በማጠናቀቅ የ2024 የርቀቱ መሪ ሰዓትና የቦታውን ክብረወሰን በማሻሻል አሸንፋለች።

በዚሁ ርቅት አትሌት ወርቅነሽ መሰለ 1 ደቂቃ ከ59 ሰከንድ ከ93ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት ሃብታም አለሙን ተከትላ መግባቷን የወርልድ አትሌቲክስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.