Fana: At a Speed of Life!

አቶ ጥላሁን ከበደ የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ሀብትነት እንዲቀየሩ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፈጥሮ ጸጋዎች ወደ ሀብትነት እንዲቀየሩ በሚደረገው ጥረት ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ጥሪ አስተላለፉ።

በአርባምንጭ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የጋሞ ዞን ተወላጆች ምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በመድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳመለከቱት፤ በርካታ የተፈጥሮ ገጸ-በረከቶች ቢኖሩም ከህዝብ ተጠቃሚነት አንጻር ክፍተቶች አሉ።

አዳጊ የሆነውን የህዝብ ፍላጎት ለማሟላትም ከመንግስት ጥረት ባሻገር ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በተለይም የሚገኙ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስት በጀት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ስለሆነም ምሁራንም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻዎች የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል።

በአመራርና ምሁራን መካከል ሊኖር የሚገባውን ግንኙነት አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን በማጠናከር የህዝብ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ችግሮችን በውይይት ለመፍታት፣ ህዝቡን በልማት ለማሳተፍ፣ የተዛቡ ነጠላ ትርክቶችን ለማረም እና ዓለም አቀፋዊ፣ ሀገራዊ፣ ክልላዊ ብሎም ዞናዊ ኢ-ተገማች ሁኔታዎችን ለይቶ ለመመከት የምክክር መድረኮች ወሳኝ እንደሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የጋሞ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ በበኩላቸው ያለውን ሀብት፣ ጉልበትና የመስራት ፍላጎት ተጠቅሞ የበለፀገ ማህበረሰብ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ለህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም በጋራ መቆም እንደሚገባ ገልጸው፤ በዚህ ላይ ሊሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.