Fana: At a Speed of Life!

ለጋዛ 200 ቶን የእርዳታ ምግብ የጫነች መርከብ በቆጵሮስ ለመቆየት መገደዷ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ሳይደረስ የረመዳን ፆም በመጀመሩ ለጋዛ 200 ቶን የእርዳታ ምግብ የጫነች መርከብ በቆጵሮስ ለመቆየት መገደዷ ተገልጿል፡፡
 
የቆጵሮስ መንግስት ቃል አቀባይ ኮንስታንቲኖስ ሌቲምቢዮቲስ ለደህንነት ሲባል መርከቧ የምትነሳበት ትክክለኛ ሰዓት ይፋ እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
 
ነገር ግን ከሰዓታት በኋላ ትንቀሳቀሳለች ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
 
የመርከቧ የመነሻ ጊዜ መዘግየት ዕርዳታውን ወደ ጋዛ ለማጓጓዝ እና ለማድረስ ግልፅ ያልሆነ ውስብስብ ሁኔታዎች መኖራቸውን ያሳያል ብለዋል፡፡
 
እስራኤል 2 ነጥብ 3 ሚሊየን ለሚሆነው የጋዛ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማቅረብ ምቹ ሁኔታዎችን አልፈጠረችም በሚል በተደጋጋሚ ክስ ቀርቦባታል።
 
ጥልቀት የሌለው የባህር ዳርቻ እና የወደቦች እጥረት እንደዚህ አይነት የባህር ላይ ስራዎችን አስቸጋሪ እንደሚያደርግም ተመላክቷል፡፡
 
በአዲሱ የባህር መተላለፊያ በኩል የሚቀርበው እርዳታ በየብስ ያለውን አስከፊ ሰብአዊ ሁኔታ ምን ያክል እንደሚደግፈውና እንደሚጎዳው ግልጽ አለመሆኑ መነሳቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
 
ይሁንና ከአምስት ወራት ጦርነት በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) በተከበበው የፍልስጤም ግዛት ሩብ የሚሆነው ህዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆኑን ገልጿል።
 
የአካባቢው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ቅዳሜ እንዳስታወቀው፤ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ህጻናትን ጨምሮ 23 ሰዎች በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ህይወታቸውን አጥተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.