Fana: At a Speed of Life!

4 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የስዊድን ኤምባሲ ተሽከርካሪ በመሸጥ የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ንብረትነቱ የስዊድን ኤምባሲ የሆነ እና አራት ሚሊየን ብር የዋጋ ግምት ያለው ተሽከርካሪ በመሸጥ የተጠረጠረ ግለሰብ ከነኤግዚቢቱ በቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ጥቁር አንበሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ስዊድን ኤምባሲ ውስጥ ነው።

ተጠርጣሪው ግለሰብ በኤምባሲው ውስጥ በሹፌርነት ሙያ ተቀጥሮ እየሠራ የነበረ ሲሆን÷ የሚያሽከረክረውን የሰሌዳ ቁጥር ኮ.ዲ 11-028 ቶዮታ ራቫ ፎር የሆነ ተሽከርካሪ ይዞ መሰወሩን የልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ወንጀል መርማሪ ዋና ሳጅን ውባለ ሻምበል ገልፀዋል።

ተሽከርካሪው መጥፋቱን ያረጋገጡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የኤምባሲው የሥራ ሃላፊዎች ለልደታ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ማመልከታቸውንም አንስተዋል፡፡

ፖሊስም የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም ባደረገው ጥረት ተጠርጣሪው በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ጎላ ሚካኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል፡፡

4 ሚሊየን ብር የዋጋ ግምት ያለውን እና ከኤምባሲው የተወሰደውን ተሽከርካሪ ለማስመለስ በተከናወነ ምርመራ የማስፋት ሥራ ተጠርጣሪው ወደ ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ በመውሰድ በ1 ሚሊየን 175 ሺህ ብር እንደሸጠውም ጠቁመዋል፡፡

አሁን ላይ መኪናው ከተሸጠበት እንዲመለስ መደረጉን ዋና ሳጅን ውባለ መናገራቸውንም የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.