Fana: At a Speed of Life!

ሀሰተኛ ኦዲት ሪፖርት በመስራት ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ፍርድ ቤት ቀረቡ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለተለያዩ ድርጅቶች ዓመታዊ ሀሰተኛ ኦዲት ሪፖርት በመስራትና ሀሰተኛ ሰነዶችን አዘጋጅተው በመጠቀም ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ ነጋሽ አህመድ እረሽድ፣ ቅድስት ሙሉጌታና ናርዶስ ብርሃኑ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋለው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ሲሆን÷ ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት አቅርቦ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

በተለይም ነጋሽ አህመድ እረሽድ በተባለው ተጠርጣሪ ላይ በተሰራው ኦፕሬሽን ስራ ግለሰቡ ‘የሂሳብ አዋቂ ነኝ’ በማለት ብቻ ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ፍቃድ ሳያገኝ በቂርቆስ ክ/ከ ወረዳ 2 እና ወረዳ 8 ስር ቢሮ በመክፈት የተለያዩ ድርጅቶች ዓመታዊ ኦዲት ሪፖርት በመስራትና ለገቢዎች ቢሮ እንዲቀርብ በማድረግ በህዝብና በመንግስታዊ ድርጅቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል መጠርጠሩን መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጠርጣሪው የስራ ቦታ በተደረገ ብርበራ በንብ ባንክ፣ በንግድና በኮንስትራክሽን ባንክ በሚል የተዘጋጀ ሀሰተኛ 3 ጥራዝ ቼክ፣ ከኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዳይሬክተር በነበሩት በአቶ የማነ ደስታ ስም ቲተርና ማህተም በማዘጋጀት፣ ሀሰተኛ ኦዲቶች እንደታደሱ ተብለው የተዘጋጁ ሰነዶች፣ ከ60 በላይ የተለያዩ ድርጅቶች ስም የተቀረጹ ማህተሞችና ቲተሮች፣ የተለያዩ የስራ ልምዶች፣ የዩኒቨርሲቲና በኮሌጆች ስም የትምህርት ማስረጃዎች ጭምር እንደተገኙ ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ገልጿል።

ከተጠርጣሪው ጋር ሲሰሩ ነበር የተባሉ ግብረዓበሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፖሊስ ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

በተጨማሪም ቅድስት ሙሉጌታ የተባለች ተጠርጣሪን የሂሳብ ሰራተኛ ሆና የተለያዩ አመታዊ ኦዲቶች ለድርጅቶች በማድረስ ጭምር ተሳትፎ አላት በማለት መጠርጠሩን የገለጸው ፖሊስ፤ ናርዶስ ብርሃኑን በሚመለከት ደግሞ ለግል ድርጅት በሚል ኦዲት ሪፖርት በማሰራት ረገድ ተሳትፎ እንዳላት ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ በተጠረጠሩበት ወንጀል የጣት አሻራ የማስነሳት ስራ ማከናወኑን የጠቀሰው መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ማለትም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት የምስክርነት ቃል መቀበልና ቀሪ ማስረጃ የማቅረብ ስራ እንደሚቀረው ጠቅሶ፤ ከወንጀሉ ውስብስብነትና ከምርመራው ስፋት አንጻር ፍርድ ቤቱ ተገንዝቦ በወ/መ/ስ/ህ ቁጥር 59/2 መሰረት የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹም ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ እንደማይገባ ገልጸው የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን እና የፖሊስ ምርመራ መዝገብን የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ተጨማሪ የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፖሊስ እንደሚያስፈልገው ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ለጊዜው በማለፍ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.