Fana: At a Speed of Life!

በቱርክ እግር ኳስ የሚስተዋሉ የሜዳ ላይ እረብሻዎች…

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራብዞን ስፖርት ደጋፊዎች የፌነርባቼ ተጫዋቾችን በጨዋታው ማጠናቀቂያ መደባደባቸውን ተከትሎ የቱርክ ሱፐር ሊግ ሌላ አሳዛኝ ክስተት አስተናግዷል፡፡

ትላንት ምሽት በፓፓራ ፓርክ የተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክርን አስተናግዶ በፌነርባቼ 3 ለ 2 አሸናፊነት ተጠናቅቋል፡፡

በ87ኛው ደቂቃ ላይ የተለያዩ ቁሶችን ወደ ሜዳ በመወርወር ሲረብሹ የነበሩት የትራብዞን ስፖር ደጋፊዎች በጨዋታው ማጠናቀቂያ ላይ የፌነርባቼ ተጫዋቾች ተሰባስበው እየጨፈሩ በነበረበት ወቅት ወደ ሜዳ በመግባት በተጫዋቾች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል፡፡

ከጨዋታው በተለቀቀው ተንቀሳቃሽ ምስልም የፌነርባቼ ተጫዋቾች የሆኑት ሚሽ ባትሽዋይ እና ኦሳይ ሳሙኤል ከደጋፊዎች ጋር ተናንቀው ሲደባደቡ የታዩ ሲሆን÷በፀጥታ አካላት ርብርብ ተጫዋቾች ሜዳውን ለቀው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡

ጉዳዩን አስመለክተው የቱርክ የሀገር ውስጥ ሚኒስትር አሊ ዩርሊካያ በሰጡት መግለጫ÷ስፖርታዊ ጨዋነት መከበር እንዳለበት ጠቅሰው በደጋፊዎች የተፈፀመው ተግባር ተቀባይነት እንደሌለው ገልፀዋል፡፡

በተጫዋቾች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ወደ ሜዳ የገቡትን ደጋፊዎች ለመለየት እና በጨዋታው መገባደጃ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለማጣራት ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የቱርክ እግር ኳስ ፌደሬሽን በበኩሉ÷ድርጊቱ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን እና በድርጊቱ ላይ የተሳተፉ ደጋፊዎች  ተጣርቶ እርምጃ እንደሚወሰደባቸው አረጋግጧል፡፡

በቱርክ ሱፐር ሊግ ቀደም ሲል የአንካራ ጉቹ  እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት ፋሩክ ኮቻ ዳኛ ኡሙት ሚለርን መደባደቡን ተከትሎ በሱፐርሊጉ ውጥረት ነግሶ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

በሶስት ወራት ውስጥ በቱርክ ሱፐር ሊግ የተፈፀሙ እነዚህ ክስተቶች በርካታ የእግር ኳስ ከዋክብት የሚገኙበትን የቱርክ እግር ኳስ ገፅታ እያበላሸው እንደሚገኝ ቢቢሲ ስፖርት አስነብቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.