Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ ዓረቢያ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ በ2 ሣምንት ውስጥ ሊጀመር ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 70 ሺህ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሦስተኛ ምዕራፍ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።

አምባሳደር ብርቱካን ይህን የገለጹት በእርሳቸው ሰብሳቢነት የሚመራው ብሔራዊ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት በሳዑዲ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመመለስ በተዘጋጀው ዕቅድ ላይ ሲመክር ነው።

ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ በብሔራዊ ኮሚቴው ውስጥ የታቀፉት የፌዴራል ተቋማት እና የክልሎችን የጋራ ቅንጅት እንደሚጠይቅም ነው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡

ከወዲሁ አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በተሟላ ሁኔታ በፍጥነት መጠናቀቅ እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።

ዜጎችን የማስመለሱ ሥራ የተሳካ እንዲሆን ከወዲሁ አስፈላጊው በጀት፣ የሎጀስቲክና አዲስ አበባ ሲደርሱ ወደየመነሻቸው እስከሚጓዙ ድረስ የሚቆዩባቸው መጠለያዎች ዝግጁ እንዲደረጉም ለባለድርሻ አካላት አስገንዝበዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዳይሬክተር ጄነራል ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን በበኩላቸው፥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት እና ክልሎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስረቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የብሔራዊ ኮሚቴው አባላት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ዕቅዱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱም አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.