Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ አዲስ አበባ ገባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋና በተካሄደው በ13ኛው የመላ አፍሪካ ጨዋታዎች የተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ዛሬ ማምሻውን አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑኩ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ አቀባበል አድርገውለታል።

የአፍሪካ ጨዋታዎች ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 14 ቀን 2016 ዓ.ም በጋና አክራ የተካሄደ ሲሆን ÷በውድድሩ ከ53 ሀገራት የተወጣጡ ከ5 ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት አይነቶች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያም በ165 ስፖርተኞች በአምስት የኦሊምፒክ ውድድሮችና አራቱ ኦሊምፒክ ያልሆኑ ስፖርቶች በድምሩ በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች ተሳትፋለች፡፡

በአትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ውሃ ዋና፣ የጠረጴዛና ሜዳ ቴኒስ፣ ቦክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌትና ወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸው የውድድር አይነቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ 9 የወርቅ፣ 8 የብር፣ 5 የነሐስ በአጠቃላይ 22 ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሁሉም የስፖርት አይነቶች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቅቃለች።

በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ለተሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን የእውቅናና የሽልማት መርሐ ግብር እንደሚካሄድም ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.