Fana: At a Speed of Life!

ነገ የሚካሄደውን የኢፍጣር መርኃ ግብር ተከትሎ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶች ይፋ ተደረጉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ነገ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ከሚካሄደው ታላቁ የኢፍጣር መርኃ ግብር ጋር ተያይዞ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችንም የአዲስ አበባ ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡

በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚካሄደው የአደባባይ ላይ የኢፍጣር መርሃ ግብር በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጀት ማጠናቀቁን የጋራ ግብረ-ሐይሉ አስታውቋል፡፡

የእምነቱ ተከታዮች ወደ ኢፍጣር መርሃግብሩ ሲመጡ ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተረድተው ትብብር እንዲያደርጉም ተጠይቋል፡፡

ከመርሃ ግብሩ ጋር የማይሔዱ በህግ የተከለከሉ እና ስለታማ ነገሮችን ይዞ መምጣት ፈፅሞ ክልክል መሆኑንም የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ሐይሉ አስታውቋል፡፡

ነገ ከሚካሄደው ኢፍጣር መርሐ ግብር ጋር ተያይዞ ከአምስት ሰዓት ጀምሮ ለተሽከርካሪ ዝግ የሚሆኑ መንገዶችንም ፖሊስ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህም መሰረት፡-

• ከመገናኛ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅ/ኡራኤል ቤ/ክርስቲያን

• ከወሎ ሰፈር ወደ መስቀል አደባባይ ኦሎምፒያ

• ከጎተራ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች ለከባድ መኪናዎች አጎና ሲኒማ፤ለሌሎች ተሸከርካሪዎች ጥላሁን አደባባይ ጋር ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡

• ከጦር ኃይሎች በሜክሲኮ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሸከርካሪዎች በተለምዶ አጠራሩ ክቡ ባንክ አካባቢ፡፡

• ከፒያሳ በቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ሐራምቤ መብራት ላይ፡፡

• እንዲሁም ከ4 ኪሎ በውጭ ጉዳይ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ብሔራዊ ቤተ መንግስት መስቀለኛው ላይ፡፡

• ከአዋሬ አካባቢ በካሳንቺስ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ኢንተርኮንትኔታል አካባቢ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ጀምሮ የኢፍጠር ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅበት ሰዓት ድረስ ዝግ የሚደረጉ ይሆናል፡፡

እንዲሁም በተገለፁት መንገዶች ላይ ተሽከርካሪን አቁሞ መሄድ እንደተከለከለ የፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኅብረተሰቡም መርኃ ግብሩ እንዲጠናቀቅ ለፀጥታ አካላት ተባባሪ እንዲሆንና አጠራጣሪ ነገር ሲያጋጥሙ በፖሊስ የመረጃ ስልኮች 0111 11 01 11 እና ነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወልና መረጃ በመስጠት ትብብር እንዲያደርግ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.