ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ወደ ልማት ገብተዋል – የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግማሽ ዓመቱ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 55 ባለሀብቶች ወደ ልማት መግባታቸውን የክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።
“በተቀናጀና ቀጣይነት ባለው የድጋፍ ማዕቀፍ አምራች ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ ታምርትና የኢንቨስትመንት መማክርት ክልላዊ የንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል።
በቢሮው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ኦሞ ሹሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ በዚህ ዓመት ክልሉ ያለውን እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት ተደርጓል።
በግማሽ በጀት ዓመቱ በተደረገው ጥረት ከ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 55 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፍቃድ በመውሰድና መሬት በመረከብ ወደ ልማት መግባታቸውን ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ ከተሰማሩባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መካከል ዘመናዊ ግብርና፣ አገልግሎት፣ ኢንዱስትሪና ሌሎችም ዘርፎች ይገኙበታል ብለዋል።
በዚህም ከ23 ሺህ 600 በላይ ለሚደርሱ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠራቸውን ገልጸው ለባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የስራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ግብርናን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለባለሃብቶች መዘጋጀቱንና የግሉ ዘርፍ እድሉን እንዲጠቀም ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።