ቀዳሚ ዓላማችን አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳካት ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀዳሚ ዓላማችን አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ሳቢ ከተማ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳካት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት መሪዎች በተገኙበት በመዲናዋ እየተካሄደ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ሥራ ሂደት ተገምግሟል፡፡
ግምገማውም በአምስት በተከፈሉት ኮሪደሮች ልማት አፈፃፀም ላይ ማተኮሩ ተገልጿል፡፡
ግምገማውን በተመለከተም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ቀዳሚ ዓላማችን አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ የተመቸች ሳቢ ከተማ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳካት ነው ብለዋል፡፡
የማልማት ሥራ ሂደቱ በግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ፣ በመንግሥት፣ አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች እና በተለያዩ አካላት የተያዙና የተከራዩ ንብረቶችን የነካ ሊሆን ቢችልም÷ ይህ ለረዥም ጊዜ ፋይዳ ትልም ይዞ የተነሳ ሥራ ሲጠናቀቅ ለሁሉም ባለድርሻ አካል ብሎም ለሰፊው ሕዝብ የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
እየተስተዋለ ያለው አዲስ የሥራ ባህል ማቆጥቆጥ በመላው ሀገራችን ሊቀዳና ሊባዛ የሚገባው ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ዐበይት የጉዞ መስመሮችን ለማሻሻል እና የከተማ ውስጥ ዝውውርን ለማሳለጥ ከፍ ያለ ግብ ያስቀመጠ ሥራ መጀመሩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
የሥራው መጠነ-ርዕይ ኢ-መደበኛ በሆነ አሰፋፈር ተጎሳቁሎ የሚገኘውን ነዋሪ የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል፣ እያደገና ከተማዋን እያጨናነቀ ለመጣው የትራፊክ ውጥረት መፍትሔ መንገዶችን ማስፋት፣ ለእግረኞች ሰፊ መንገዶችን ማበጀት፣ የቅርስ ቦታዎችን መጠገን ብሎም ሕንጻዎችን በከተማዋ የሕንጻ ሥነ-ውበት ደረጃ ልክ ማድረስ የሚሉ ተግባራትን ያቀፈ መሆኑም ተብራርቷል፡፡
ከሥራው አስቀድሞም የከተማዋ አሥተዳደር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማካሄዱ እና በልማት ሥራውም የተነሱ ነዋሪዎችን ለመርዳት የተለያዩ ተግባራትን ማከናወኑ ተጠቅሷል፡፡
የኮሪደሮች ልማት ሥራ የዝናቡ ወቅት ከመግባቱ አስቀድሞ በሚቀጥሉት ወራት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል ተብሏል፡፡