ከ750 በላይ ለሚሆኑ በሰሜኑ ጦርነት የንግድ ስራቸው ለተጎዳባቸው ሴቶች የሚውል የገንዘብ ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ፣ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች በጦርነት ምክንያት በንግድ ስራቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን ሴቶች ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ፕሮጀክቱ ሴቶች በተለያዩ የገቢ ማስገኛ መስኮች በመሰማራት የኢኮኖሚ አቅማቸውን ከማሳደግ ባለፈ ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ እገዛ እንደሚያደርግ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ገንዘቡ በዩኤንዲፒ አማካኝነት በክልሎቹ በኩል እንደሚተላለፍ እና በመጀመሪያው ዙርም 750 ሴቶችን ስራ ለማስጀመርና ተጠቃሚ ለማድረግ ለእያንዳንዳቸው 500 ዶላር ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
ድጋፉ በስድስት ወራት ውስጥ በዩኤንዲፒ አስተባባሪነት፣ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ፣ ከዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ኤጀንሲ፣ ከጃፓን እና ከግብረሰናይ ድርጅቶች የተሰበሰበ ከ400 ሺህ ዶላር በአጠቃላይ ከ22 ሚሊየን በላይ በሆነ ገንዘብ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ከታላቁ ሩጫ የተሰበሰበውን 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብርን ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ተረክበው በኢትዮጵያ ለዩኤንዲፒ ተወካይ ሳሙኤል ዲው አስረክበዋል።
ፕሮጀክቱም በቀጣይ ስድስት ወራት የሚቀጥል ሲሆን ÷ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ዩኤንዲፒ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ሰነድም ተፈራርመዋል።
በማህሌት ተ/ብርሃን