Fana: At a Speed of Life!

የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ መፍጠሪያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአካባቢ ጥበቃ ግንዛቤ መፍጠሪያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር “ብክለት ይብቃ ውበት ይንቃ “በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል ።

ንቅናቄውን በይፋ ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንዳሉት÷ ድህነትን ማሸነፍ የሚቻለው ከተፈጥሮ ጋር መታረቅ ሲቻል ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተሰራው ስኬታማ ሥራ ከተፈጥሮ ጋር እንድንቀራረብና የማህበረሰቡን ግንዛቤ ያሰፋ የለውጡ ሂደት አንዱ ማሳያ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአካባቢ ብክለት ችግር ለመቋቋም ከአረንጓዴ አሻራ በተጨማሪ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ ዘመናዊ የእርሻ ዘዴ፣ የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ እየሰራች እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

ይህም በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመው÷ ሁሉም አካል በየደረጃው ንቅናቄውን እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ንቅናቄው ለስድስ ወራት የሚቆይ ሲሆን÷ በየወሩ የተለያዩ የአካባቢ ብክለትን የሚያስከትሉ ችግሮች ላይ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የግንዛቤ መፍጠር ሥራ ይሰራል ተብሏል።

በዚህም መሰረት ግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሩ በየወሩ የፕላስቲክ ብክለት፣ የአየር ብክለት፣ የውሃ ብክለት፣ የአፈር ብክለት እና የድምፅ ብክለት ላይ ትኩረቱ እንደሚያደርግ ተመላክቷል፡፡

በምንተስኖት ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.