Fana: At a Speed of Life!

በበልግ ወቅት ከመደበኛ ያለፈ ዝናብ ስለሚኖር ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበልግ ወቅት ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ መጠን ሊኖር ስለሚችል ይህን ተገንዝቦ ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

የያዝነው ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ሲዳማ እና ሶማሌ ክልሎች እንዲሁም በጉጂና ቦረና ዞኖች የዝናብ ወቅት መሆኑን በኢንስቲትዩቱ የሚቲዎሮሎጂ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አሳምነው ተሾመ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

በሰባት ክልሎች ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች መለየታቸውን እና ጥናት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹት ደግሞ በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውኃ ሃብት አሥተዳደር ዘፍር ሚኒስትር ዴዔታ አብርሃ አዱኛ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ሰሞኑን ሊኖር ከሚችለው ከመደበኛ ያለፈ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች ሊከሰት የሚችልን የመሬት መንሸራተት ታሳቢ ያደረገ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አረጋግጠዋል፡፡

በመንግሥት ከሚከናወኑት ሥራዎች በተጨማሪም ሕብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋኦ በማድረግ ከፍተኛ ዝናብ ከሚያስከትላቸው አደጋዎች እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡

በሐይማኖት ወንድራድ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.