ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በደቡብ ሱዳን ለሚሰማሩ ከፍተኛ መኮንኖች ሽኝት ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በደቡብ ሱዳን ለሚሰማሩ የኢትዮጵያ ፖሊስ ከፍተኛ መኮንኖች ሽኝት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሽኝት ፕሮግራሙ ላይ እንደገለጹት÷የኢትዮጵያ ፖሊስ ሠራዊት በሥነ-ምግባሩ እና በወታደራዊ አቅሙ በዓለም አቀፍ ተቋማት ተፈላጊ እና ተመራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡
የፖሊስ መኮንኖቹ በስምሪታቸው የኢትዮጵያ ፖሊስ አሁን የደረሰበትን ደረጃ የሚያመላክት የላቀ ሥነ-ምግባርና ፖሊሳዊ ሙያ ሊያሳዩ እንደሚገባ ማስገንዘባቸውንም የፌዴራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል።
መሰል ዓለም አቀፍ ተሳትፎ የሚጠይቁ ሥራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው÷ ለሰላም አስከባሪ ተጓዦች ተልዕኳቸው የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።
የፌደራል ፖሊስ ሰላም ማስከበር ማዕከል ሃላፊ ኮማንደር ተገኝ አጋዥ በበኩላቸው ÷ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳንና በአብዬ ግዛቶች እንዲሁም በሐይቲ የተሰማሩ የፌደራል ፖሊስና የክልል ፖሊስ አመራሮች የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት በመወጣት የሀገራቸውንና የተቋማቸውን መልካም ገጽታ መገምባታቸውን ተናግረዋል፡፡