Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደስታ ሌዳሞ ለፊቼ-ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ የሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ለሆነው ፊቼ-ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት መልዕክት አንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የሲዳማ ህዝብ በርካታ ባህሎችና ትውፊቶች ባለቤት ሲሆን የዘመን መለወጫ ፊቼ-ጫምባላላ በዓል አንዱ ነው።

ፊቼ-ጫምባላላ በዓል ለህዝቡ የጥበብ ጥግ፣ ለኢትዮጵያ ኩራትና እንቁ ባህላዊ ቅርስ ነው። ፊቼ- ጫምባላላ በሲዳማ ብሔር የአዲስ ዓመት ዘመን መለወጫ በዓል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ ባህላዊ ትውፊትም ነው።

ሲዳማ የራሱ የሆነ ጊዜን፣ ወቅትንና ዘመንን የሚቀምርበት ባህላዊ እውቀትና ጥበብ ያለው ህዝብ ሲሆን÷ይህን ባህላዊ እውቀቱንና ጥበቡን ከትውልድ ወደ ትውልድ እያሸጋገረ ለዚህ ትውልድ አድርሶታል።

የሲዳማ አባቶች ባህላዊ የስነ ፈለክ ምርምር እውቀትና ጥበባቸው የረቀቀ ሲሆን ከዋክብትን የፀሐይንና የጨረቃን ውህደትንና ተናጠላዊ አንድምታን በመመርመር የወቅቶችን እርዝማኔና ንባሬ በማጥናት ሽርፍራፊ ሰከንዶችን፣ ደቂቃዎችንና ሰዓታትን ቀምረው ቀናትን፣ሳምንታትን፣ ወራትንና አመትን የሚለኩበት የሲዳማን የቀን አቆጣጠር ካላንደር የፈጠሩ ናቸው።

ያኔ ዓለማችን በመናዊ የሳይንስ እውቀትና ቴክኖሎጂ ባልረቀቀበት ዘመን አብዛኛውን የዓለማችን ህዝቦች ንቃተ ኅሊናቸው ባላደገበት ዘመን፤ በጥንታዊ ኋለቀር የአኗኗር ስርዓት ዘመን ቀደምት የሲዳማ አባቶች የሰማይን ተፈጥሮዋዊ ምንነት፣ የምድርን አቀማመጥ፣ የከዋክብትንና የጨረቃ ሥርዓትና ውሁደት መርምረውና አጥንተው ይሄው ለዛሬው ትውልድ ይህን የቀንና የጊዜን መለኪያ ባህላዊ ጥበብ አድርሰዋል።

የሲዳማ ባህላዊ የቀን አቆጣጠር ጥበባዊ እሴት ትንታኔ በዓለም አቀፍ ቅርስነት መመዘኛዎች የሚመጥን ሆኖ በመገኘቱ በዓለም አቀፍ ቅርስነት በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስ ሊመዘገብ አስችሎታል፡፡

በተጨማሪም የዓለም የጋራ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ከሚደረግላቸው እና እውቅና ካገኙ ዓለም አቀፍ ቅርሶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።

በበፊቼ -ጫምበላላ በዓል ለተፈጥሮ እፅዋትና ስነ ምህዳር ልዩ እንክብካቤና ጥበቃ የሚያደረግ፣ የሴቶችና ሕፃናት መብት የሚከበርበት፣ ለደን፣ ለአፈና ለውሃ ጥበቃ እንዲሁም ለተፈጥሮ የሚሰጠው ክብር የላቀ በመሆኑ እነዚህ ባህላዊ እሴቶች ተተንትነው ፊቼ -ጫንባላላን በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ካስቻሉት ነጥቦች የተወሰኑቱ ናቸው።

ፊቼ -ጫምባላላ ከአሮጌው አመት ወደ አዲስ ዓመት መሸጋገሪያ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን÷በዓሉ ሲከበር ቂምና በቀል ይዞ ወደ አዲሰ ዘመን መሻገር ስለማይፈቀድ የሲዳማ ህዝብ በሁሉቃ ስርዓት ቂም፣ ቁርሾና በቀሉን በይቅርታ የሚያወርድበት በዓል ነው።

በፊቼ -ጫምባላላ ህዝቡ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን በማቅረብ አቃፊነትፈቱን የሚያንፀባርቅበት፣ በህብረተሰቡ መካከል ወንድና ሴት ተብሎ የፆታ ልዩነት የማይደርግበት፣ህፃንና አዋቂ ተብሎ ሳይከፋፍል ሁሉም በአንድ አይን የሚታይበትና ለእንስሳት ልዩ እንክብካቤ በመስጠት በዓሉ የሚከበርበት ዕለት ነው።

በፊቼ -ጫምባላላ ለህፃናትና ለታዳጊ ወጣቶች ልዩ ትኩረት የሚሰጥ በመሆኑ ልጆች ምንም ዓይነት ሥራ የማይሰሩበትና በደስታ እንዲቦርቁበት የሚደረግበት ጊዜም ነው።

ፊቼ- ጫምባላላ ለሲዳማ ብሔረሰብ ተወላጅ ብቻ ሳይሆን አብሮ በሚኖረውም ማህበረሰብ ዘንድ ትልቅ እንድምታ የሚሰጠው ሲሆን÷ህዝባዊ ፍቅር የሚገለፅበት፣ የተጣሉ የሚታረቁበት እንዲሁም የሰላምና የልምላሜ መገለጫም ጭምር ሆኖ ይቆጠራል።

አኩሪ የሆነውን ደማቅ ባህለዊ ትውፊት በማጉላት አሁንም እንደ ቀድሞው ያጡትን በመደገፍና በመርዳት፣ የአካባቢያችንንና የቀያችንን ሰላም በመጠበቅ ከክፋትና ከአስፀያፊ ተግባር ራሳችንን አቅበን በዓሉን በደስታ እያከበር ወደ አዲሱ ዘመን እንሸጋገር እላለሁ።

በድጋሚ እንኳን ለሲዳማ ብሔር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል በሰላም አደረሰን!

መጋቢት 26 ቀን 2016 ዓ.ም

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.