አቶ አሻድሊ ከዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካና የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አሻድሊ ሀሰን ከዓለም አቀፍ የምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካና የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ክሪስ ኒኮይ ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸውም÷ በግጭት ምክንያት በክልሉ ለተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥታዊ ካላሆኑ ድርጅቶች ጋር በመሆን መንግሥት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አቶ አሻድሊ አስረድተዋል፡፡
አሁን ላይ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ 90 በመቶ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል፡፡
የምግብ ድጋፍን ጨምሮ የመልሶ ማቋቋምና የወደሙ ተቋማት ግንባታ ሥራ በመንግሥት አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ የዓለም ምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፋቻውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሱዳን ያለውን ግጭት ሸሽተው ወደክልሉ የገቡ ስደተኞችን ተቀብሎ በማስተናድ ረገድም በክልሉ ያለው ጫና ቀላል እንዳልሆነ ማስገንዘባቸውን የርዕሰ መሥተዳድር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ክሪስ ኒኮይ በበኩላቸው ከተፈናቃዮችና ከሱዳን ከመጡ ስደተኞች ጋር በተያያዘ በሚቀርበው ድጋፍ ላይ ጫና መኖሩን እንደሚገነዘቡ ጠቅሰው ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡