Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከምዝበራ ማዳን መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን የፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በአስቸኳይ ሙስና መከላከል ዘርፍ ያከናወናቸውን ተግባራት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

በኮሚሽኑ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል መሪ ሥራ አስፈጻሚ ገዛኸኝ ጋሻው እንዳሉት፤ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ መሥሪያ ቤቶችና ሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ የአስቸኳይ ሙስና መከላከል ተግባራት ተከናውነዋል።

በዘርፎች፣ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች 373 የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ መሰራቱን ጠቅሰው፤ በዚህም በዘጠኝ ወራት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ከምዝበራ ማዳን መቻሉን ገልፀዋል።

የከተማና የገጠር መሬት ወረራ ከምዝበራ በመከላከል ረገድ ከ22 ሚሊየን 288 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ብለዋል።

በንብረት ማስወገድ፣ ግዥ፣ መሬት ያላግባብ ለመስጠት መሞከር፣ የእርዳታ እህል ሥርጭትና ሕግን ያልተከተለ የሠራተኛ ቅጥር የሙስና ድርጊት ሊፈጸምባቸው ከነበሩና የተደረሰባቸው ድርጊቶች መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የሕዝብና የመንግሥት ኃብትና ንብረቶችን በመታደግ ረገድ ለተገኘው ውጤት የኅብረተሰቡንና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ትብብር አድንቀው በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.