የግብርናና ምግብ ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የግብርናና ምግብ ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለማልማት የሚያስችለው ሁለተኛው ዙር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈረመ፡፡
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው እና በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ሚስተር ጋንተር ቤገር መካከል ተፈርሟል፡፡
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ሶስት የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን አቅም ለማጎልበት እና ለመደገፍ የሚውል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ እንዲሆን ዩኒዶ የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
በስምምነቱ ወቅት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታዋ ሰመሪታ ሰዋሰው÷ ድጋፉ መንግስት የግብርና፣ የኢንዱስትሪ እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎችን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት ያግዛሉ ብለዋል፡፡
የዩኒዶ ዳይሬክተር ሚስተር ጋንተር ቤገር በበኩላቸው÷ ዩኒዶ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡