Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ መሳብ የሚያስችል የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ጸደቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ኢንቨስትመንትን በቀላሉ ለመሳብ፣ የአምራች ዘርፉን ለማበረታታት እና የውጭ ንግድ አቅምን ለማሳደግ የሚያስችል የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው ረቅቅ አዋጅን አስመልክቶ የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች እና የንግድ እና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ አዋጁን ያጸደቀው፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አማረች ባካሎ (ዶ/ር)÷አዋጁ የግሉ ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ በግብርና፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሳተፍ ለማበረታታት ያለመ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም ዓቀፍ የንግድ ሰንሰለት ላይ የሚኖር ቁርኝትን ማስፋት እና ዘላቂ እድገትን ማምጣት የረቂቅ አዋጁ አላማ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የልዩ ኢኮኖሚ ዞን መርሐ ግብርን ቀልጣፋ እና አመቺ የኢንቨስትመንት እና የንግድ ከባቢያዊ ሁኔታ ለመፍጠር ረቂቅ አዋጁ እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ አዋጁ እስካሁን ተግባራዊ የተደረገውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስርዓት ዲዛይንና ትግበራ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ስርዓት በማሳደግ የኢኮኖሚውን መሰረት ለማሳደግ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን ከፍ ለማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አዋጅ ቁጥር 1 ሺህ 322/2016 ሆኖ በሙሉ ድምጽ የጸደቀው የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ጠንካራ የአሰራር ስርዓት፣ ጠንካራ ቁጥጥር እና አደረጃጀት እንዲኖር እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የበይነ መንግስታት የልማት ባለስልጣን (ኢጋድ) ማቋቋሚያ ስምምነት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን አስመልክቶ የቀረበውን አዋጅ መርምሮ አጽድቋል፡፡

የሚሻሻለው አዋጅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም፣ ለቀጣናው የተሻለ ለውጥና አሰራርን የሚሰጥ መሆኑን የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገልጿል፡፡

አዋጁ የሀገራቱን ግንኙነት የበለጠ እንደሚያጠናክር እና የግንኙነት ዘርፎችን እንደሚያሰፋ የተገለጸ ሲሆን÷ የስምምነት ማሻሻያ አዋጁን ኢትዮጵያ ማጽደቋ መንግስት እየሰራ ያለውን ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችለዋል ተብሏል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር እያደረገች ያለውን ጥረት እንደሚደግፍ እና ጠንካራ ቀጣናዊ ድርጅት ለመመስረት እንደሚረዳ ተጠቁሟል፡፡

 

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.