Fana: At a Speed of Life!

ለውጭ ባለሀብቶች ተከልክለው የቆዩ የንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች ክፍት ሊደረጉ ነው

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለውጭ ባለሀብቶች ተከልክለው የቆዩ የገቢና ወጪ፣ በጅምላ እና በችርቻሮ ንግድ ስራዎች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ሊደረጉ መሆኑ ተገለፀ፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በጋራ በሰጡት መግለጫ÷ ለበርካታ አመታት ብዙዎቹ የገቢ፣ የወጪ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ የንግድ ስራ መስኮች ለውጭ ባለለብቶች ተሳትፎ ተከልክለው መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ይህም የሆነው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ውድድር ጫና እንዲጠበቁ በማድረግ ካፒታል እንዲያፈሩ እድል ለመስጠትና በውስጥ አቅም ላይ የተመሰረተ ዘላቂ ኢኮኖሚ የመገንባት አላማን በመያዝ እንደነበር የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርዓያ ሥላሴ በመግለጫው ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ዘርፎቹን የመዝጋት ፖሊሲ በተገቢው መጠን የሚፈለገውን አላማ ከማሳካት አንፃር ክፍተቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል።

በመሆኑም የሀገርንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ተከልክለው የቆዩ የንግድ ኢንቨስትመንት መስኮች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።

በዚህም መሰረት የፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ የውጭ ባለሀብቶች መሳተፍ የሚችሉበት መመሪያ መፅደቁን ተናግረዋል።

በመመሪያው መሰረትም የውጭ ባለሀብቶች ቅድመ ሁኔታዎችን እስካሟሉ ድረስ በጥሬ ቡና፣ በቅባት እህሎች፣ ጫት፣ ጥራጥሬ፣ ቆዳና ሌጦ፣ ዶሮና የቁም እንስሳት መላክ የወጪ ንግድ ላይ መሳተፍ ይችላሉ ነው የተባለው።

ገቢ ንግድን በተመለከተም ከማዳበሪያና ነዳጅ በስተቀር በሁሉም የገቢ ንግድ ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራት የሚችሉ ሲሆን÷ በጅምላ ንግድ ደግሞ ከማዳበሪያ ጅምላ ንግድ በስተቀር መሳተፍ ይችላሉ ተብሏል።

በችርቻሮ ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች በተመለከተ ደግሞ በሁሉም የችርቻሮ ንግድ መሠማራት እንደሚችሉ ተመላክቷል።

የንግድ ዘርፉ ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት መደረጉ የንግድ ስርዓትን በማዘመን፣ ለሸማቾች በሸቀጦች ዋጋ ቅናሽ እና እንደሀገርም ኢኮኖሚን ከማሳደግ አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታል ተብሏል።

መመሪያው የተፈለገውን ዓላማ እንዲያሳካም በርካታ ተቋማትን ያካተተ ቋሚ የጋራ ኮሚቴ እንደሚደራጅም ተመላክቷል።

በሳሙኤል ወርቃየሁ እና አሸናፊ ሽብሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.