Fana: At a Speed of Life!

ያለፉት 6 ዓመታት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ድል የተገኘበት ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን አስጠብቃ መጓዝ የቻለችባቸው እና ዲፕሎማሲያዊ ድሎች የተገኙባቸው ናቸው ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ያለፉት 6 የለውጥ ዓመታት የዲፕሎማሲ ሥራዎች በፈተና የታጀቡ አንፀባራቂ ድሎች የተገኙበት ነው ብለዋል፡፡

በኢኮኖሚ መስክ ማሻሻያዎችን በማድረግ ለውጭ ኩባንያዎች ዝግ የነበሩ መስኮችን በመክፈት፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትን በማሳደግ እና በዋናነት ደግሞ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎችን በአብነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን የተሠራው የዲፕሎማሲ ስራ ትልቅ ስኬት የታየበት መሆኑን ነው የገለጹት።

ለአየር ንብረት የማይበገር ኢኮኖሚን ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ሀገር አቀፍ ጥረት በአረንጓዴ አሻራና ዲፕሎማሲ ሥራዎች ታግዞ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ መሰራቱን ተናግረዋል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋር መልካም ጉርብትናን ለማጠናከር እና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጎልበት የተሰሩ ስራዎችን አንስተው÷እነዚህ የዲፕሎማሲ ሥራዎች በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና እድገትን ለማዝለቅ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ገልፀዋል።

የውጭ ተፅዕኖ እና ጣልቃ ገብነትን አጥብቆ በመከላከል መንግስት እና ህዝብ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እና በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል በነበረው ግጭት የሀገርን ጥቅም አስጠብቆ ማዝለቅ እንደተቻለ መጥቀሳቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካዊ ማዕቀፍ እንዲፈታ ባላት ያላሰለሰ ጥረት እና ፍላጎት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በመፈረም እና ገቢራዊ እንዲሆን በማስቻል ሀገሪቱ ለሰላም ያላትን ፅኑ ፍላጎት አስመስክራለች ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ መስራች በሆነችባቸው የባለብዙ ወገን ተቋማት ውስጥ ተሳትፎዋን በማጠናከር በተለይ በፀጥታው ም/ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድምፅ እያሰሙ ካሉ መሪ ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነችም ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.