የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደርን ለመደገፍ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት መቅረፁን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የታክስ አስተዳደርን ለመደገፍ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገለፀ፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ በፕሮጀክት አተገባበር ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሤ ÷ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በ2022ዓ.ም ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ተገንብቶ ሃገራዊ ወጪ በታክስ ገቢ ተሽፍኖ የማየት ራዕይ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ራዕይ ከግብ ለማድረስ እንደ ዓለም ባንክ ካሉ ዓለምዓቀፍ ተቋማት ጋር አብሮ መሥራት ትልቅ አቅም ይፈጥራል ያሉት ወ/ሮ ዓይናለም ሚኒስቴር መ/ቤቱም ይህ በዓለም ባንክ ተቀርጾ ሥራውን በይፋ ሲጀምር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል፡፡
የዓለም ባንክ ተወካይ የሆኑት ራጁ አዋስቲህ በበኩላቸው ÷የኢትዮጵያ መንግስት ዘመናዊ የታክስ አስተዳደርን ለማስፈን የሚያደርገውን ጥረት ድርጅታቸው በበጎ ጎን እንደሚመለከተው እና ይህንንም ጥረት ለመደገፍ የአምስት ዓመታት ፕሮጀክት ቀረጾ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በይፋ ሥራውን ሲጀምር በተለያዩ መስኮች ላይ ድጋፍ ለመስጠት ውጥን መያዙን የተናገሩት ተወካዩ መስኮችም የተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ ሴት ግብር ከፋዮችን መደገፍ፣ የግብር ከፋዮችን መብት አስመልክቶ ግንዛቤ መስጠት ዋና ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በፕሮጀክቱ አተገባበር እና አፈጻጸም ዙሪያ መሠል ውይይቶች የሚካሄዱ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን÷ ይህ እንደተጠናቀቀም ፕሮጀክቱ ሥራውን በይፋ ይጀምራል መባሉን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡