Fana: At a Speed of Life!

ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶችን ለሚስተዋሉ ግጭቶች መፍትሔ ማድረግ እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶችን በማልማት ለሚስተዋሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲሆኑ ለማድረግ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አመላክቷል፡፡

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የ9 ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትን አድምጧል፡፡

የጤና፣ ማህበራዊ ልማት ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርቱን ካደመጠ በኋላ የባህል ማዕከላት ግንባታዎችና ሀገር በቀል እውቀቶች ልማት አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ ባህላዊ እሴቶችንና ሐይማኖታዊ ትውፊቶችን የሚሸረሽሩ መጤ ባህሎችን፣ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል በባህሉና በማንነቱ የሚኮራ ትውልድን በመገንባት ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ለምን አልተሰራም ሲል ጠይቋል፡፡

ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶችን በማልማት በኢትዮጵያ ለሚስተዋሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲሆኑ ለማድረግ ከተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት የሚጠበቀውን ውጤት ለምን ማምጣት አልተቻለም? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ በወቅቱ እንደገለጹት÷ያሉ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የሚረዱ ስልቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመንደፍ እና ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓቶችን በማጎልበት የበጀት አመቱን ቀሪ ስራዎች ለማከናወን ይሰራል፡፡

በተለይም የቋንቋ ፖሊሲ የትርጉም ስራዎችን የማጠናቀቅ፣ የፊልም ፖሊሲ ማስተግበሪያ ስትራቴጂዎችን የመተግበር እንዲሁም አገር አቀፍ የኪነ ጥበብ ፈጠራ ውድድሮችን ማካሄድ በቀጣይ በትኩረት የሚሰራባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

መለስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን እንደተሞክሮ በመውሰድም በየደረጃው በማስፋፋት ህብረተሰቡ በስፋት በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፍባቸውን መድረኮች የማሳደግ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ለቴክኖሎጂም ለምርምርም የሚሆኑ ሀገር በቀል እውቀቶች እንዳሉም የተገለጸ ሲሆን÷ሃብቶችን ጠብቆ ከማቆየት አንጻር ተቋሙ እየሰራ ነው ተብሏል፡፡

ባህላዊ የእርቅና የሽምግልና ስርዓቶችን በማልማት ለሚስተዋሉ ግጭቶች መፍትሔ እንዲሆኑ ለማድረግም ከዚህ በፊት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሚኒስቴሩ የሥራ ሀላፊዎች ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል፡፡

ያሉ ችግሮችን ለመፍታትከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መስራትም እንደሚያስፈልግ ሃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በየሻምበል ምሕረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.