Fana: At a Speed of Life!

ከ337 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ337 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው ተገለጸ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን ከሚያዚያ 11 ቀን እስከ ሚያዚያ 17 2016 ዓ/ም ባደረገው ክትትል 286 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዛቸው ተነግሯል፡፡

50 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የወጭ፤ በድምሩ 337 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት፣ የቁም እንስሳት፣የጦር መሳሪያ እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ጅግጅጋ፣ ድሬዳዋ እና አዳማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ ፥ በቅደም ተከተላቸውም 108 ሚሊየን፣ 63ሚሊየን እና 36 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻላቸውም ነው የተገለጸው፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ ተይዘዋል ተብሏል፡፡

ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሠባት ተጠርጣሪዎች እና ስድስት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ከኮሚሽኑ ማህበራዊትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ አካላት ምስጋና አቅርቧል፡፡

የኮንትሮባንድና ንግድ ማጭበርበር የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.