Fana: At a Speed of Life!

እየተገኙ ያሉ ስኬቶች በተግባር የክልሉን ሕዝብ ማሻገር አለባቸው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሁሉም ዘርፍ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች በተግባር የክልሉን ሕዝብ ማሻገር መቻል አለባቸው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ባለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የክልሉ የ2016 በጀት ዓመት 3ኛ ሩብ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ግምገማ የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል፡፡

አቶ ሽመልስ በመድረኩ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በገቢ አሰባሰብ፣ ያሉ አቅሞችን አሰባስቦ በመጠቀም፣ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ አመራር በመፍጠር፣ ሕዝብን አስተባብሮና ንቅናቄዎችን ፈጥሮ በመሥራት ረገድ ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል።

ይህንንም ተቋማዊ ማድረግና ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት የነበሩ ስኬቶች ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጉዞ የሚጠናክሩ መሆናቸውን አንስተው በአንጻሩ ክፍተቶችም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያለማከናወን፣ በዞኖች መካከል ያሉ የአፈፃፀም ልዩነቶች፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር፣ ከወረዳ በታች ያለው የአመራር መዋቅር ጠንካራ አለመሆን፣ ስርቆትና የውሸት ሪፖርቶች እንዲሁም ችግሮችን ለሌላ አካል የመስጠት አዝማሚያዎች በቀጣዩ ሩብ ዓመት እንዲታረሙ ሲሉ አሳስበዋል፡፡

4ኛው ሩብ ዓመት ወሳኙና ፈታኙ ጊዜ መሆኑን ጠቁመው÷ ያላለቁና የተንጠባጠቡ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በክልሉ በሁሉም ዘርፍ እየተገኙ ያሉ ስኬቶች በተግባር የክልሉን ሕዝብ ማሻገር መቻል እንዳለባቸውም ነው ያስረዱት፡፡

በመራኦል ከድር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.