የመንግስትና የግል ተቋማት ሠራተኞች በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት እና የግል ተቋማት ሠራተኞች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ጠየቀ።
የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ካሳሁን ፎሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ135ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ49ኛ ጊዜ “ለሰላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሄ እንሻለን” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን በማስመልከት ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም ኮንፌዴሬሽኑ ሰራተኛው የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣና ጥያቄዎቹም እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ በሠራተኛው ዘንድ ሲጠየቁ የነበሩ ጥያቄዎች በሒደት ምላሽ እያገኙ ቢሆንም አሁንም ያልተመለሱ እና ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ አንስተዋል።
ለዚህም ኮንፌዴሬሽኑ ከሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ለሀገሪቱ በርካታ ችግሮች መፍትሄ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አውስተዋል፡፡
በየትኛውም ተቋማትና ዘርፎች ላይ የተሰማሩ ሠራተኞች ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሚያዚያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተለያዩ የፓናል ውይይቶች እንደሚከበር መጥቀሳቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።