Fana: At a Speed of Life!

የኮሪደር ልማት ሥራውን በፍጥነት አጠናቅቆ ለሕዝብ ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከክረምት በፊት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ።

የኮሪደር ልማት ግንባታ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ምክትል ከንቲባው÷ ሥራው በተያዘው ፍጥነት ከቀጠለ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አመላክተዋል፡፡

የከተማ አሥተዳደሩ አመራሮችና ለሥራው የተቋቋመው አስተባባሪ ኮሚቴ ሂደቱን በመገምገም ሥራዎች በፍጥነት እንዲሄዱ በትጋት እየሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በልማት ሥራው ለተነሱ ነዋሪዎችም የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ መስሪያ ቦታና ምትክ መሬት የመስጠት እንዲሁም የካሳ ክፍያ እየተፈጸመ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በኮሪደር ልማቱ፣ በመልሶ ማልማት፣ በአረንጓዴና ከተማ ውበት ዘርፎች በቋሚነት ለ1 ሺህ 485 እና በጊዜያዊነት ለ13 ሺህ 784 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ሲጠናቀቅም በእነዚህ ቦታዎች ከመልሶ ማልማት በፊት ተፈጥሮ የነበረውን የሥራ ዕድል በ51 መቶ እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም የከተማዋን ገቢና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት በመጨመር ብሎም በከተማዋ የስማርት ሲቲ አገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር መሰረት እንደሚጥል ነው ያመላከቱት፡፡

የኮሪደር ልማት ሥራው የሚከናወንባቸው አካባቢዎችም÷ ከአራት ኪሎ ፒያሳና የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ ከአራት ኪሎ ዐደባባይ በእንግሊዝ ኤምባሲ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ሳር ቤት በጎተራ ወሎ ሰፈር ዐደባባይ፣ ከአራት ኪሎ መስቀል ዐደባባይ እና ቦሌ ድልድይ፣ በመገናኛ አስከ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን/ ኤግዚቢሽን ማዕከል መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.