Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን ርዕሳነ መሥተዳድሮች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር በቀል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መሥተዳድሮች ገለጹ፡፡

ንቅናቄው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በጥራትና በብዛት ለማምረት እንዲሁም የግብርና እና ማዕድን ምርቶች ላይ ዕሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር ኢ/ር) ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የፋብሪካዎች ምርታማነት ማደጉን እና ትላልቅ የውጭ ኢንቨስተሮችም በማምረቻው ዘርፍ እንዲሰማሩ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡

ክልሉ በግብርና ዘርፍ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆን የፍራፍሬ፣ ቅመማቅመም፣ የማርና እንስሳት ተዋፅዖ ምርት እምቅ አቅም ስላለው የአካባቢው ማኅበራት ዕሴት የሚጨምር የምርት ማቀነባበር ሥራ ጀምረዋል ብለዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በየክልሉ የሥራና የሀገር ምርትን የመጠቀም ባህል ላይ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በግብርና ምርት ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ 74 ኢንዱስትሪዎች ድጋፍ ተደርጎላቸው በሙሉ አቅም ወደ ማምረት መግባታቸውንም አንስተዋል፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ÷ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ኢንቨስትመንት፣ የኢንዱስትሪና ከተማ ልማትን ጨምሮ በሌሎችም ሴክተሮች የሚታይ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተዘግተው የቆዩ 10 ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው÷ ይህም በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ዘርፍ በርካቶች እንዲሰማሩ ማስቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ እንደገለጹት÷ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለድርሻ አካላትን ጠንካራ የኢንዱስትሪ ልማት ቅንጅት የፈጠረና የዘርፉን ማነቆዎች የፈታ ነው፡፡

ንቅናቄው በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ የጨውና ኬሚካል ኢንዱስትሪን ጨምሮ ከ100 በላይ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

የኃይል አቅርቦት፣ የመሠረተ-ልማት ግንባታና የፋይናንስ አቅርቦትን ለማሟላት በአንድ ማዕከል የባለድርሻ አካላት ትብብር ለችግሮች ሁነኛ መፍትሔ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አምራች ኢንዱስትሪዎች የኃይል፣ የፋይናንስ፣ የመስሪያ ቦታ፣ የመሰረተ ልማት እጥረትና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር እንደነበረባቸው ያስታወሱት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ደስታ ሌዳሞ÷ በ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄ አማካኝነት ችግሮቹን ማቃለል መቻሉን አስረድተዋል።

የካፒታል እጥረት ላለባቸው ኢንዱስትሪዎችም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር የብድርና የግብዓት አቅርቦት በማመቻቸት የተሻለ ሥራ መሥራት ተችሏል ብለዋል፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው÷ በክልሉ የ’ኢትዮጵያ ታምርት’ ንቅናቄን በመጠቀም የአምራች ኢንዱስትሪ ልማትን ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ ንቅናቄውን ተከትሎ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት ለኢንዱስትሪ ልማት አመቺ ቦታዎችን  የመለየትና የማዘጋጀት ተግባር መከናወኑንም ጠቅሰዋል።

በክልሉ የሚገኙ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም የሀገር ውስጥ ምርቶችን እንዲጠቀሙ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.