Fana: At a Speed of Life!

በብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር ይሰራል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀገር ባለቤቶች እንዲሆኑና በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚሠራ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ አመራሮች በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ/ፕሮፋይል ጥናት ፕሮጀክት ላይ ተወያተዋል፡፡

አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በውይይት መድረኩ፥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነቶች ተጠንተው ተግባራዊ መደረጋቸው የኢትዮጵያን አንድነት፣ ወንድማማችነትና እኩልነት ለማጽናት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡

ምክር ቤቱም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሀገር ባለቤቶች እንዲሆኑና በሕዝቦች መካከል ጤናማ ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለብዙ ዘመናት እንደድርና ማግ ተሳስረው የኖሩ ሕዝቦች እንደሆኑ አስታውሰው፥ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብዛት፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ማኅበራዊ መስተጋብር ምን እንደሚመስል ማጥናትና ለትውልድ ማስተላለፍ ሕዝቦች ያሉበትን ሁኔታ በትክክል አውቆ የሚገባቸውን ጥበቃ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ጥናቱ በሕዝቦች መካከል ያለው መከባበርና አንድነት እንዲጠናከር፣ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት መገለጫ የሆኑት ነባር ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ታሪኮችና እምነቶች እንዲጠኑና ተግባራዊ እንዲደረጉም አሳስበዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሐንስ አድገህ፥ በኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትኖግራፊና የቋንቋ አትላስ/ፕሮፋይል ጥናት አነሳሽ ምክንያቶች፣ ጥናቱን ለማስጀመር የነበረውን ውጣ ውረድ እና ጥናቱ ተጠናቆ ተግባራዊ ሲሆን ለሀገር የሚያበረክተውን ፋይዳ በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የባህልና ማኅበራዊ ጥናት ተማራማሪ የሆኑት ዶ/ር ባይለየኝ ጣሰው በበኩላቸው፥ ሀገራችንን እና ራሳችንን ካወቅን የምናደርገውን እናውቃለን ማለታቸውን ከምክር ቤቱ ያገነነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.