Fana: At a Speed of Life!

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 87ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በገንዘብ ሚኒስቴር የቀረቡትን የተለያዩ የብድር ስምምነቶች የማጽደቂያ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው መሆኑ ታውቋል፡፡

ሁለቱ የብድር ስምምነቶች የተደረጉት ከኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር ሲሆን አላማቸውም ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እና ለኮሮና ቫይረስ የሕክምና መገልገያ መሳሪያዎች አቅርቦት ማስፈጸሚያ የሚውሉ ናቸው፡፡

ሶስተኛው የብድር ስምምነት ከዳንስኬ ባንክ ኤ.ስ ጋር የተደረገ ሲሆን ለአሰላ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል ነው፡፡

ሶስቱም የብድር ስምምነቶች አነስተኛ ወለድ የሚታሰብባቸው (ከ1% በታች)፤ የረጅም ጊዜ እፎይታ ያላቸው እና በ40 ዓመታት ተከፍለው የሚጠናቀቁ በመሆኑ ከአገራችን የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን በማረጋገጥ ይጸድቁ ዘንድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

ሀገራዊና አካባቢያዊ ሰላም፣ ደህንነትና ጸጥታ፣ ብሄራዊ መግባባት፣ በሀገረ-መንግስት እና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ እንዲሁም የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ቀጠናዊ ትስስር እና ትብብር ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ፤ በተጨማሪም ቁልፍ በሆኑ ፖሊሲዎች ላይ ጥናቶች በማካሄድ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ፣ ስትራተጂያዊ እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንተና መስጠትና ለውሳኔ የሚረዱ የቅድሚያ ግምቶች ማሳየት፣ የዳታ ክምችትና የእውቀት ቋቶችን ማደራጀት ከኢንስቲትዩቱ የሚጠበቁ ተግባራት ናቸው፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

የኢንቨስትመንት ረቂቅ ደንብ ሌላው ምክር ቤቱ የተመለከተው ጉዳይ ነው፡፡

በቅርቡ ከጸደቀውን የኢንቨስትመንት አዋጅ በአግባቡ ለማስፈጸም ይቻል ዘንድ እንደዚሁም በአጠቃላይ የኢንቨስትመንት ህግ ማእቀፉ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶች በግሉ ዘርፍ ሊሳተፉ የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመከለስ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ሲያቀርብ፡፡

በተጨማሪም በሥራ ፈጠራን ለማበረታታት እንዲሁም በቴክኖሎጂ እና በክህሎት ሽግግር ላይ ያለውን ሚና ማሳደግ፣ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙትን የመንግስት አገልግሎቶች በመሰብሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት፣ የኢንቨስትመንት አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመን፣ የኢንቨስትመንት ማነቆ ለሆኑ ጉዳዮች መፍትሔ በመስጠት የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረግ፣ እንዲሁም ግልጽ እና ውጤታማ የባለሀብቶች ቅሬታ የሚስተናገድበት ሥርዓት ማበጀት በሚያስችል መልኩ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ረቂቅ ደንብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማከል ተቀብሎ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.