Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ በኮቪድ-19 ሳቢያ የኑሮ ችግር ሊገጥማቸው የሚችሉ ዜጎችን ለመታደግ የሚያስችል ስልት ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሳቢያ የኑሮ ችግር ሊገጥማቸው የሚችሉ ዜጎችን ለመታደግ የሚከናወነውን የገቢ ማሰባሰብ ስራ ለማጠናከር የሚያስችል ስልት መዘጋጀቱን የከተማው አስተዳደር የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ ወይዘሮ ፍቅርተ ነጋሽ እንደገለጹት፥ በከተማው አስተዳደር በቀረበው ጥሪ መሰረት በመዲናዋ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሳቢያ የኑሮ ችግር ሊገጥማቸው የሚችሉ ዜጎችን ለመታደግ የድጋፍ ማሰባሰብ ስራው ሲከናወን ቆይቷል።

የገንዘብ ድጋፉ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክና በዳሽን ባንክ በተከፈቱ የትረስት ፈንድ ሂሳቦች በኩል ገቢ ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል።

የንጽህና መጠበቂያ ምርቶች፣ የአልባሳት፣ ምግብ ቁሳቁሶችና ሌሎች የአይነት ድጋፎችም በከተማ አስተዳደሩ የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽህፈት ቤት በኩል መሰባሰቡንም አክለዋል።

እንደ ሀላፊዋ ገለጻ፤ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተደረገ የሀብት ማሰባሰብ 230 ብር ሚሊየን በጥሬ ገንዘብና 400 ሚሊየን ብር ግምት ያለውን ድጋፍ በአይነት ማሰባሰብ ተችሏል።

ሆኖም በመዲናዋ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በመጨመሩና የገቢ ማሰባሰብ ስራውም እየተቀዛቀዘ በመምጣቱ የህብረተሰቡን ተሳትፎ ለማጠናከር የሚያስችል የማነቃቂያ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ነው የገለጹት።

የተዘጋጀው ረቂቅ ስትራቴጂ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት ከጸደቀ በኋላ በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶች ተግባራዊ እንደሚደረግም ወይዘሮ ፍቅርተ ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከል ስራዎች ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላት ታሳቢ ያደረገ የንቅናቄ ስራ ለመስራት መታቀዱንም አክለዋል።

ቀደም ሲል በከተማ አስተዳደሩ የማህበራዊ ትረስት ፈንድ ጽህፈት ቤት ሲካሄድ የነበረው የገቢ ማሰባሰቢያ ስራም በ4 ኪሎ አካባቢ ወደ ሚገኘው የወወክማ ማዕከል መቀየሩንም ሀላፊዋ መጠቆማቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.