ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከጉራጌ ልማት ማህበር አባላት ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ ከተመራው የጉራጌ የልማት ማህበር አባላት ጋር ተወያይተዋል።
የጉራጌ ልማት ማህበር አባላት በከተማዋ አጠቃላይ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ በሚችሉበት ሁኔታ ዙሪያ ነው ውይይቱ የተደረገው።
ኢንጂነር ታከለ ኡማ በውይይቱ ላይ እንዳሉት የልማት ማህበሩ አባላት በአዲስ አበባ የተጀመረውን ፈጣን እድገት ለመደገፍ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያርግ ገልጸዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በበኩላቸው፥ የልማት ማህበሩ አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ከማህበራዊ አገልግሎት ባለፈ በልማት ስራዎች ላይ በመሳተፍ እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ የደቡብ ክልል መንግስት እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡
የልማት ማህበሩ አባላት በቀጣይ በከተማዋ ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡
የጉራጌ ልማት ማህበር አባላት ባለፈው ክረምት ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።