አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በ7 ግለሰቦች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ እንዲያሻሽል ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጠ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፍርድ ቤቱ አቶ እስክንድር ነጋን ጨምሮ በ7 ግለሰቦች ላይ አቃቤ ህግ ያቀረበውን ክስ እንዲያሻሽል ትእዛዝ ሰጥቷል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ወንጀል ችሎት አቃቤ ህግ ከዚህ በፊት የመሰረተው ክስ አጠቃላይ ዋስትና ላይ ዝርዝር ክሱን ተመልክቶ ውሳኔ ለማሳረፍ ክሱ ሊሻሻል ይገባል ሲል አዟል።
በዚህም አቃቤ ህግ የሚያሻሽለው በሰኔ 23 እና ሰኔ 24 2012 ዓ.ም በሰው ላይም በንብረት ላይም ደረሰ የተባለው ጉዳት ተለይቶ እንዲቀርብ፣ የደረሰው ጉዳት ቦታው የት እንደሆነ፣ በየት ክፍለ ከተማ እና ወረዳ፣ በስንት ሰዓት የሚለው መገለፅ አለበት ያለው ፍርድ ቤቱ፤ ቦታው ከታወቀ በኋላም የተከሳሾቹ የወንጀል ተሳትፎ በዝርዝር ተለይቶ እንዲቀርብ አዟል።
በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ በሳምንት ውስጥ ክሱን አሻሽሎ እንዲቀርብ ለመስከረም 19 2013 ዓ.ም ጠዋት በችሎት እንዲያቀርብ አዟል።
በችሎቱ የተገኙት የእነ አቶ እስክንድር 4 ጠበቆች ማረሚያ ቤት ከቤተሰብ ጋር እያገናኛቸው እንዳልሆነ፣ ምግብና ልብስም እየገባላቸው አይደለም ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
ሌሎች አቤቱታዎችንም እናቅርብ ያሉት ጠበቆቹ፤ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችሁ በችሎት ተመዝግቦ የሚሄድ አይደለም፤ ክርክር አንዳይነሳበት ሲል ጊዜ የማይሰጡ የህክምና እና በቤተሰብ መጎብኘት ያለባቸውን ማረሚያ ቤቱ እንዲፈፅም ትእዛዝ ሰጥቷል።
በተከሳሾች በኩልም የተለያዩ የመብት አቤቱታዎች ለችሎቱ አቅርበዋል።
በሌላ ዜና በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ የክስ መዝገብ የቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች በተከሰሱበት በአዋጅ ከተሰጣቸው ስልጣን ውጪ ሰዎችን በመያዝና በማሰር ስልጣንን ያለ አግባብ መገልግል ወንጀል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ጀምሮ የነበረው ከመጋረጃ በስተ ጀርባ ምስክር የማሰማት ሂደት ቀጥሏል።
ከሰዓት በነበረውን ረጅም ሰዓታትን የፈጀ በአቃቤ ህግ በአንድ የመጋረጃ ጀርባ መስክር የቀጠለ ሲሆን፥ በተከሳሽ ጠበቆች በኩል እየቀረበ በነበረው መስቀለኛ ጥያቄ በሰዓት ምክንያት ሳይጠናቀቅ ለመስከረም 19 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ