Fana: At a Speed of Life!

የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡን አስመልክቶ በሚሊኒየም አዳራሽ የምስጋና እና ዕውቅና መድረክ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ ሲ) የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ሆኖ መመዝገቡን በማስመልከት በሚሊኒየም አዳራሽ የምስጋና እና ዕውቅና መድረክ ተካሂዷል።
 
በመድረኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ እና ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ጨምሮ የሌሎች ሃይማኖት መሪዎች፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና የእምነቱ ተከታዮች ታድመዋል።
 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፥የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ሆኖ በመመዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
 
በዓሉ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች መዝገብ ውስጥ እንዲሰፍር የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ላበረከቱት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርቲያን እና መንግስት እንዲሁም ለእምነቱ ተከታዮች እና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስጋና አቅርበዋል።
 
የጥምቀት በዓልበ በዩኔስኮ መመዝገቡም የቤተ ክርስቲያኒቱን፣ የሀገራችንና የሕዝባችን ስም በዓለም ላይ ደምቆና ጐልቶ እንዲታወቅ የሚያደርግ መሆኑን አውስተዋል።
 
ከዚህ ባለፈም የዓለም ህዝብ ኢትዮጵያን የማወቅ ፍላቱን በመጨመር ሀገሪቱን በቱሪዝም ዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን የሚያስቸል መሆኑን አብራርተዋል።
 
በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች የጥምቀት በዓልን ሃይማኖታዊ ቀኖናውን እና ባህሉንና በጠበቀ መልኩ ማክበር እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው፥የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ሆኖ በመመዝገቡ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
 
የጥምቀትን በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ለማስተዋወቅም የከተማ አስተዳድሩ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት አስፈላጊውን ትብብር የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
በዚህ መሰረትም የታቦት ማደሪያ ስፍራዎችን የማጽዳት እና የማስዋብ ስራ እንደሚከናወን የገለጹት ምክትል ከንቲባው፥የከተማው ነዋሪዎችም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
 
ከየትኛውም እምነት አስተምህሮ ውጪ ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ እንዲሁም የእርስ በርስ ግጭትን የሚያነሳሱ አካላትን በቅንጅት መከላከል እንደሚገባም አንስተዋል።
 
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፥ የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ የማይዳሰስ የባህል ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን የምስል እና ድምፅ ማስረጃዎችን በማቅረብ ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
 
ቅርሱ እምነታዊ ስርዓቱን ተጠብቆ እና ለምቶ እንዲቀጥልም የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
 
የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የጥምቀት በዓል አከባበር በዓለም የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ መወሰኑ ይታወቃል።
 
በዚህ መሰረትም የጥምቀት በዓል ከመስቀል፣ ከገዳ ሥርዓት እና ፍቼ ጨምበላላ በዓላት በመቀጠል በኢትዮጵያ አራተኛው የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዝግቧል።
 
በሳራ መኮንን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.