Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ድርጅቶችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ላይ በትኩረት ልትሰራ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የተቃረበችው ኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ድርጅቶች ተወዳዳሪነትን ማሳደግ ላይ በትኩረት ልትሰራ እንደሚገባ የኢኮኖሚ ምሁራን ተናገሩ።

ኢትዮጵያ  በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እያደረገችው ያለው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትኩረት ከሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ ሀገሪቱን የአለም የንግድ ድርጅት አባል ሀገር ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ማፋጠን ነው።

ሀገሪቱ የድርጅቱ አባል መሆኗ ዘርፈ ብዙ ትሩፋት እንደሚያመጣላት ነው የኢኮኖሚ ምሁራኑ የሚናገሩት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ምሁራን የሆኑት ዶክተር ታደለ ፈረደ እና ፕሮፌሰር አለማየሁ ከፋና ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥  ኢትዮጵያ የአለም ንግድ ድርጅት  አባል  መሆኗ  የተረጋጋ የንግድ ስርዓት እና ፖሊሲ እንዲኖራት ለማድርግ የከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም ሀገሪቱ አስተማማኝ እና በቂ  ኢንቨስትመንትን እንድትስብ እና የሀገር ውስጥ አምራቾች አለም አቀፍ ገበያውን እንዲቀላቀሉ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የአለም የንግድ ድርጅት አባል ሆነች ማለት የገቢ ሸቀጦች ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ይገባሉ ማለት አይደለም የሚሉት ዶክተር ታደለ፥የቀረጥ ቅነሳው ወይም ዜሮ ቀረጥ ውሳኔው በሂደት የሚሆን ነው ባይ ናቸው።

አባል መሆን የንግድ ስርዓት ግልፅነትን ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል እንጂ የቀረጥ ጉዳይ በሀገራት የሁለትዮሽ ድርድር የሚወሰን መሆኑንም አስታውሰዋል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ስትራቴጂክ የሆኑ ዘርፎችን በመለየት ከቀረጥ ነፃ የሚደረጉት የትኞቹ ናቸው የሚለውን በግልፅ ማስቀመጥ ነው የሚሉት ዶክተር ታደለ፥የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ሊተኮርበት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፕሮፌሰር አለማየሁ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኩባንያዎች  አለም አቀፍ ውድድሩን ይቋቋሙታል ወይ የሚለው በዝርዝር ጥናት ሊደረግበት እንደሚገባ  ይናገራሉ።

በእያንዳንዱ ዘርፍ የኩባንያዎቹ አቅም እና ድክመት ሳይጠና ወደ አለም የንግድ ድርጅት  እንደማይገባም ያብራራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ሀላፊው ዶክተር ዘርአየሁ ስሜም፥ አስቀደመው ጥናት ሳያደርጉ ሁሉንም ነገር ክፍት ያደረጉ ሀገራት የሸቀጥ ማራገፊያ ሆነው መቅረታቸውን አንስተዋል።

በተለይም የእስያ እና ላቲን አሜሪካ ሀገራት  የዚህ ችግ ተጋላጭ መሆናቸውን በመግለፅ እኛም ከዚህ ልንማር ይገባል ነው ያሉት ዶክተር ዘርአየሁ።

ኢኮኖሚ ውስጥ ፅንፍ የያዘ አካሄድ አያዋጣም ያሉት ዶክተር ዘርአየሁ የሀገር ውስጡንም ሆነ የውጭ ኩባንያዎች ያጣጣመ አካሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በተለይም የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን ተወዳዳሪነት ማሳደግ ላይ ሊታሰብበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.