የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተያየት ˝ስርዓት የሌለው እና አደገኛ ነው˝- ጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላት
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ከህዳሴ ህድብ ጋር ተያይዞ ለግብፅ ወግነው የሰጡትን አስተያየት ጥቁር አሜሪካውያን የኮንግረስ አባላት ስብስብ የሆነው ብላክ ኮከስ አወገዘ።
የስብስቡ አባላት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ፥ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በሚያካሂዱት የሶስትዮሽ ድርድር ላይ ገለልተኛ እንድትሆን አሳስቧል።
የፕሬዚዳንቱ አስተያየት በሀገራቱ መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ እንደሚያደርግ የገለፀው ብላክ ኮከስ የዶናልድ ትራምፕን አስተያየት እንደሚያወግዝም አስታውቋል።
ብላክ ኮከስ በፈረንጆቹ 1971 የተመሰረተ ሲሆን የጥቁር አሜሪካውያን እና ሌሎች የተገለሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚሰራ ነው።
ህብረቱ የአሜሪካ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሴኔት አባል የሆኑ ጥቁሮችን የያዘ ነው።