Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችን ይዘው የተገኙ 37 መድሃኒት ቤቶች ታሸጉ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት እና የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን በከተማዋ ጥፋት የተገኘባቸው 37 መድሃኒት ቤቶች እና መደብሮችን ማሸጉን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በከተማዋ ከሚገኙ ከ1 ሺህ በላይ የመድሃኒት ቤቶች እና የመድሃኒት መደብሮች ውስጥ በ350 መድሃኒት ቤቶች ላይ ባካሄደው ድንገኛ ዘመቻ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው እንደሚገኙበትም አስታውቋል።
በዚህም 90 የሚሆኑ መድሃኒት ቤቶች እና መደብሮች የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ነው የተነገረው።
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ደብረወርቅ ጌታቸው እንደገለፁት መድሃኒት ቤቶቹ እና መደብሮቹ ሊታሸጉ እና የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው የቻለው መጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችን ይዘው በመገኘታቸው ነው።
ምንጫቸው ያልታወቀ መድሃኒቶችን ይዘው መገኘታቸው፣ እጥረት ያለባቸው መድሃኒቶችን መደበቅ፣ የማይሰሩ ማቀዝቀዣዎች እንዲሁም ቴርሞሜትሮችን ለይምሰል አስቀምጠው በመገኘታቸው እንዲታሹ ተደርገዋልም ነው ያሉት።
ከዚህ ባለፈም እነዚህ መድሃኒት ቤቶች ያለ ሀኪም ማዘዣ መድሃኒቶችን በመሸጥ እና ከፀረ ተባይ መድሃኒቶች ጋር መድሃኒቶቹን ቀላቅለው ሲሸጡ መገኘታቸውን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
ለዚህ ዘመቻም ከባለስልጣኑ ሰራተኞች ባሻገር በ8864 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ የሰጡ ዜጎች አስተዋፅኦ የጎላ እንደነበርም ተጠቁሟል።
በፀጋዬ ንጉስ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.