ዶክተር አብርሃም በላይ የትግራይ ልዩ ሀይልና ሚሊሺያ በፌደራል መንግስትና በአማራ ክልል መንግስት የተደረገለትን የሰላም ጥሪ በሙሉ እምነት እንዲቀበል አሳሰቡ
አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 25 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በበርካታ ግጭቶች ውስጥ በስውርም ሆነ በግልፅ በአፍራሽ ተልእኮ እጁን ሲያስገባ ቆይቷል አሉ የብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ፡፡
የህወሓት የጠላፊ ቡድን በትናንትናው ምሽት የሰላም ሀይል በሆነውና የትግራይ ህዝቦች ደጀን በመሆን ለአመታት ዋጋ እየከፈለ ባለው የአገር የመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ በወሰደው አሳፋሪ የጥቃት ትንኰሳና ዝርፊያ መነሻነት የፌደራሉ መንግስት መጠነ ሰፊ ህግ የማስከበር እርምጃ ለመውሰድ ተገድዷልም ብለዋል፡፡
ይህ በአይነቱና በታሪክም ፍፁም እንግዳ የሆነ የክህደት ተግባር ለአገራቸው አንድነትና ክብር ለአመታት መስዋእትነት ለከፈሉ ህዝቦች ይህ ጠላፊ ቡድን ያለውን ንቀት ያሳየበትና በዚህ የለየለት እብደቱም የአገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ የጣለ በመሆኑ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃዎች በሙሉ እየተወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል ዶክተር አብረሃም በማህበራዊ ገፃቸው በኩል።
ሰላማዊው የትግራይ ልዩ ሀይልና ሚሊሺያም በፌደራል መንግስቱ እና በአማራ ክልል መንግስት የተደረገለትን የሰላም ጥሪ በሙሉ እምነት እንዲቀበልም አሳስበዋል፡፡
በአጎራባች የአማራ ክልሎች በመሻገር ወንድሙ ከሆነው የአማራ ህዝብ ጋር በሰላም እንዲቀላቀልና ከአካባቢው መስተዳድር አካላት ጋር በቅርበት በመስራት ፈጣን ሰላማዊ ሽግግር ለማስፈን የሚያስችል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግስት ሰላምና መረጋጋትን በመላው ትግራይ ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የህግ ተግባራትን በመደበኛው የህግ አግባብ ለማስፈፀም አዳጋች መሆኑን ከግምት ውስጥ በመክተት በዛሬው እለት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ለስድስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል።
በዚህ ቡድን በአገር ላይ የተቃጣውን የክህደት ተግባር መላው የትግራይ ህዝብ ከመከላከያ ሰራዊትና ከመላው የአገራችን ህዞቦች ጋር በጋራ በመቆም በፅናት እንድትመክቱና ይህንን አስከፊ የክህደት ተግባርም በጥብቅ በማውገዝ ቀናኢ ኢትዮጵያዊነታችሁን በድጋሚ በማረጋገጥ ታሪካችሁን እንድታድሱ የአደራ መልእክቴን አስተላልፋለሁ ብለዋል።