አቶ ወርቁ አይተነው ለመከላከያ ሰራዊት እና ለአማራ ልዩ ሀይል 100 ሰንጋዎችንና 200 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለሃብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና ለአማራ ልዩ ሀይል 100 የስጋ በሬዎችንና 200 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ድጋፍ አደረጉ።
ድጋፉን የባላሃብቱ ተወካይ አቶ ሲሳይ ታደሰ በጎንደር ከተማ ተገኝተው ለሎጂስቲክ ኮሚቴው አስረክበዋል።
ተወካዩ ባለሃብቱ አሁን ያደረጉት ድጋፍ ጊዜያዊ እንደሆነና መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር በድል እስከሚያጠናቅቅ ድረስ በቀጣይ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ ማለታቸውን ከማዕከላዊ ጎንደር ዞን ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ድጋፉን የተረከቡት የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የጎንደር ቀጠና ሎጂስቲክ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ባንቲሁን መኮንን በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊት ከክልሉ ልዩ ሃይልና የሚሊሻ አባላት ጋር በመሆን በተለያዩ ግንባሮች እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለማገዝ ባለሃብቱ ያደረጉት ድጋፍ ከመንግስትና ከሃገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መቆማቸውን ያሳዩበት ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ በጅማ ዞን የጌራ ወረዳ ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የ28 ሰንጋዎችን ድጋፍ አድርገዋል።
ድጋፉን የወረዳው ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሃሺምና አባገዳዎች በኢፌዴሪ ምድር ሃይል ተገኝተው አስረክበዋል።
በወረዳው ነዋሪዎች የተደረገውን ድጋፍ የተረከቡት የመከላከያ ህብረት ሎጂስቲክ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሜጀር ጄኔራል አብዱራህማል እስማኤል አሎ ፤ የተደረገው ድጋፍ ለሰራዊቱ ሞራል በመሆን ግዳጁን በአጭር ጊዜ እንዲያጠናቅቅ ያስችለዋል ብለዋል።
በተያያዘም የጅማ ከተማ ነዋሪዎች “የሀገር መከላከያ ሠራዊታችንን መርዳት ሀገራችንን መርዳት ነው” በሚል መሪ ቃል ለሃገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ድጋፉን የከተማዋ ባለሀብቶች፣ የትራንስፖርት ማህበራት፣የታክሲ እና የባጃጅ አሽከርካሪዎች፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የንግድ ማህበረሰብ፣ ታዋቂ ግለሠቦች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ያደረጉት፡፡
በዚህም በጥሬ ገንዘብ 4 ሚሊየን 368 ሺህ 660 ብር እንዲሁም በቁሣቁስ ደግሞ ከ20 በላይ የጭነት አይሱዙ የተለያዩ የምግብ ግብዓቶችን አበርክተዋል፡፡
ካደረጉት ድጋፍ ባለፈም በቀጣይ አራት ሚሊየን ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡