Fana: At a Speed of Life!

ስደተኞችን እንደ መሳሪያ መጠቀምና ለግጭት ተግባር ማዋል በዓለም አቀፍ ሕግ ያስጠይቃል – የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ

አዲስ አበባ፣ህዳር 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስደተኞችን እንደ መሳሪያ መጠቀምና ለግጭት ተግባር ማዋል በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ አስታወቀ።
ኤጀንሲው በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራዊያን ስደተኞች ጉዳይ እንዳሳሰበው አመልክቷል።
ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል በሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎም መንግስት ለአገር መከላከያ ሰራዊት የሕግ ማስከበርና አገርን የማዳን ተልዕኮ የሰጠ ሲሆን ሰራዊቱም የተሰጠውን ተልዕኮ በመፈጸም ላይ ይገኛል።
ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ግን “የኤርትራ ወታደሮች ከመንግስት ጋር በመሆን ወጉኝ” ብሏል።
የአገር መከላከያ ሰራዊትም በቡድኑ የተነሳው ሀሳብ ፍጹም ውሸት የሆነና “ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን” በአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ የመከላከያ ሰራዊቱንና የኤርትራ ወታደራዊ የደንብ ልብስ አስመስሎ በመስራት ራሱ እየፈጠረ ያለው ድራማ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም ቡድኑ ያስታጠቃቸው ሃይሎች እየተሸነፉ መሆኑን ሲያውቅ ያለበሰውን ሬንጀር በማስወለቅ በአሮጌ ጫማና በባዶ እግራቸው እንዲዋጉ በማድረግ ሠራዊቱ ንጹሃን ዜጎችን እየተዋጋ ነው የሚል የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጨ መሆኑንም አመልክቷል።
የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳዮች ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና ሞደርናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ በአካል ንጉሴ ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ በ1951 በጄኔቫ የጸደቀውን የስደተኞች ኮንሼንሽን እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1977 በኒውዮርክ የጸደቀውን የስደተኞች ፕሮቶኮል ተቀብላ በማጽደቅ ተግባራዊ እያደረገች ነው።
በእነዚህ ዓለም አቀፍ ሕጎች ኢትዮጵያ ለስደተኞች የምግብ፣ የጤናና ማህበራዊ አገልግሎትን መስጠት እንዲሁም ደህንነታቸውን የመጠበቅ ግዴታ አለባት ብለዋል።
ኢትዮጵያ ተቀብላ የምታስተናግዳቸው ስደተኞች በመጠለያዎችና በከተማ ውስጥ የሚኖሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ግጭቶች አለመረጋጋቶች ሲኖሩ ስደተኞች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለአደጋ እንደሚጋለጡ ተናግረዋል።
መንግስት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር እርምጃ እየወሰደ ቢሆንም በፌዴራልና በትግራይ ክልል መንግስት መካከል ያለው የግንኙነት መስመር በመቋረጡ መረጃዎችን በሚፈለገው ፍጥነት ለማግኘት ፈታኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይሁንና በተለያዩ መንገዶች በተደረጉ ማጣራቶች “ክልሉን እመራዋለው የሚለው አካል” በከተማ የሚኖሩትን የኤርትራ ስደተኞች ወደ መጠለያ አስገድዶ እያስገባ መሆኑን ኤጀንሲው መረጃ እንደደረሰው ጠቅሰዋል።
“በትግራይ ያለው ታጣቂ ሃይል” ስደተኞችን በከለላነት ተጠቅሞ ሰለባ እንደማያደርጋቸው እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ነው አቶ በአካል የገለጹት።
ስደተኞችን እንደ መሳሪያ መጠቀምና ለግጭት ተግባር ማዋል በዓለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ተግባር ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ሕግ ስደተኞች የሚኖሩባቸውን ካምፖችና ስደተኞችን እንደ ጋሻና ከለላ መጠቀም ክልክል መሆኑንና ይሄን የሚያደረግ አካል በወንጀል እንደሚጠየቅ ተናግረዋል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.