Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ንጹሃንን የገደሉ 16 የህወሃት ተላላኪ ሃይሎች ተደመሰሱ- የክልሉ ፖሊስ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በትናንትናው ዕለት አገር አቋራጭ አውቶብስ አስቁመው ንጹሃን ሰዎችን የገደሉ 16 የህወሃት የጥፋት ተልእኮ አስፈጻሚ ሽፍታዎች መደምሰሳቸውን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ።

የዞኑ የጥፋት ሃይሎች በትናንትናው ዕለት ከወምበራ ወደ ግልገል በለስ ሲጓዝ የነበረ አውቶብስ በቡለንና ድባጤ ወረዳዎች መካከል ቂዶ በሚባል ቦታ አስቁመው ጥቃት መፈጸመዋቸውን የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት መግለጹ ይታወሳል።

በጥቃቱ የንጹሀን ሕይወት ሲያልፍ በዞኑ የዲባጤ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል።

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ እንዳሉት፥ በአካባቢው የሚገኘው የሀገር መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ባደረጉት የተቀናጀ እንቅስቃሴ ለንጹሃን ሞት ምክንያት የሆኑ 16 የህወሓት የጥፋት ትልዕኮ አስፈጻሚዎች ተደምስሰዋል።

ሌሎች ሁለት ደግሞ በሕይወት መያዛቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ፥ ቀሪዎችን ተከታትሎ የመደምሰስ ስራ መቀጠሉን አስታውቀዋል።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙት ደግሞ አካባቢውን የማረጋጋት ስራ እያካሄዱ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

በዞኑ ጸጥታ የማስከበር ሥራ እየሠራ የሚገኘው ኮማድ ፖስት ትላንት በንፁሀን ላይ በተፈጸመው ጥቃት ትክክለኛውን የሟቾችን ቁጥር እያጣራ እንደሚገኝ የገለጹት ኮሚሽነር አብዱልአዚም፥ ኮማንድ ፖስቱ በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሚሰጥ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.