የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ገለጹ
አዲስ አበባ ፣ ህዳር 7 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ዙሪያ በየደረጃው ባሉ የአስተዳደር እርከኖች ሲካሄድ የነበረው ውይይት ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል፡፡
በማጠቃለያ ውይይቱ ላይ የተገኙት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
የህወሓት ጁንታ ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የጥፋት ሀይሎችን በማሰማራት በበርካታ ንፁሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በማውገዝ በጋምቤላ ክልልም መሰል ተግባራትን እንዳይፈጽም አካባቢያቸውን ነቅተው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል፡፡
በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሀገሪቱን ህግ ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ሀሳባቸውን እንዲገልፁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት የጥፋት ቡድኑን ለህግ ለማቅረብ መንግስት የህግ ማስከበር ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው የክልሉ ህብረተሰብ ከሰራዊቱ ጎን በመቆም ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን ለተለያዩ አካላት የሚያቀርበው የእንደራደር ጥያቄ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ገልፀዋል፡፡
የተጀመረው ህግን የማስከበር ዘመቻ ውጤት እስከሚገኝበት ድረስም ለሰራዊቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መላው የክልሉ ህብረተሰብ በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡