Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከኬንያ ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር ተወያዩ።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ የቀጠናው ሀገራት መንግስት የጀመረውን ህግና ህገ መንግስት የማጽናት ጥረት እንዲደግፉ የጠቅላይ ሚንስትሩን መልዕክት ለፕሬዚዳንቱ አድርሰዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ተኩል ሲካሄድ ስለቆየው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ እንቅስቃሴ፤ ይህ ለውጥ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስላስገኛቸው ትሩፋቶች በዝርዝር አብራርተዋል።

አቶ ደመቀ የህውኃት አጥፊ ኃይሎች መንግስት የጀመረውን የለውጥ ሂደት ለማጨናገፍ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደነበረ ጠቅሰው መንግስት በሆደ ሰፊነት በተለያዩ መንገዶች ለማግባባት እና በትዕግስት ለመያዝ መሞከሩን አስረድተዋል።

ይሁንና እነዚህ የህውኃት ጽንፈኛ ቡድን የመንግስትን ትዕግስት ከምንም ባለመቁጠር አገሪቱን ወደ ትርምስና ብጥብጥ እንድታመራ በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ቡድኖችን በገንዘብና በሎጂስትክ ሲደግፍና ሲያደራጅ መቆየቱን፤ በዚህም ሂደት የበርካታ ዜጎች ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።

ይህ አልበቃ ብሎ ሰሞኑን በሰሜን የአገራችን ክፍል የሰፈረውን ሰሜን ዕዝ ከኋላ መውጋታቸውንና ብዙዎችን መግደላቸው፤ ይህ ደግሞ በሃገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ በመሆኑ እነዚህን አጥፊዎች ወደ ህግ ለማምጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን፤ እንቅስቃሴው የኢትዮጵያን ህዝብ ከነዚህ አጥፊዎች ለመታደግ እንደሆነና ይህም የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በስፋት ገልጸዋል።

ፕሬዝደንት ኡሁሩም ሲናገሩ ኢትዮጵያና ኬንያ የሰላም መልህቅ መሆናቸውንና ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አረጋግጠው በተፈጠረው ነገር ማዘናቸውን እና የተጀመረው የህግና ስርዓት የማስከበር ተግባር በተቻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቅ ገልጸዋል።

አቶ ደመቀ ከፕሬዚዳንት ኡሁሩ ጋር ከመወያየታቸው ቀደም ብሎ ከኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ጋርም ተወያይተዋል፡፡
ፕሬዝደንት ሙሴቪኒ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔ ምልክት እና የነጻነት ተምስሌት መሆኗን ጠቅሰው፤ ለአፍሪካ ሃገራትም እንደተምሳሌት የምትታይ ሃገር መሆኗን አንስተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠር ማንኛውም ነገር በአህጉሩ ላይ እንድምታ የሚኖረው በመሆኑ እንደማይቀበሉትና የተጀመረው ህግን የማስከበር ሂደት በአፋጣኝ መጠናቀቅ እንዳለበትም ነው የተናገሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.