Fana: At a Speed of Life!

ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል የ196 ሰንጋዎች እና 230 በግና ፍየሎች ድጋፍ ተረከበ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 10 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህግ በማስከበር ዘመቻ ላይ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል 196 ሰንጋዎችና 230 በግና ፍየሎች ድጋፍ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ ተረከበ።
የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ምሽት ላይ በህወሓት ጁንታ የደረሰበትን ጥቃት በመመከት ሕግ የማስከበር ሥራውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል።
የቡድኑ እኩይ ተግባር ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን ድርጊቱን ከማውገዝ በተጨማሪ ለሰራዊቱ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዛሬው እለትም ከኦሮሚያ ክልል የሆለታ፣ ሰበታ፣ አዳማና ሌሎች አካባቢዎች ማህበረሰቡ ያዋጣቸውን 196 ሰንጋዎችና 230 በጎችና ፍየሎች በተወካዮቻቸው አማካኝነት አስረክበዋል።
ድጋፉን ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሁም የአዳማ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልጀሊል አብዱሬ በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ በመገኘት አስረክበዋል።
በአገር መከላከያ ሰራዊት የራያ አካባቢ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ይመር መኮንን የህወሃት ጁንታ የፈጸመውን የክህደት ድርጊት ተከትሎ እየተካሄደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
ለተመዘገበው ውጤትም የሕዝቡ አለኝታነትና ደጀንነት ሰራዊቱን በእጅጉ ያኮራ መሆኑን ጠቅሰው ጁንታውን በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲሚያቀርቡት አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወርቅሰሙ ማሞ፤ “የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ሩቅ ተጉዘው ሰራዊቱን ለመደገፍ መምጣታቸው የህወሃትን ጁንታ ለህግ ለማቅረብ በጋራ መቆማችንን የሚያሳይ ነው” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.