“ከተማችንን ከቆሻሻ ፣ሃገራችንን ከጁንታ፣ ከከሀዲነትና ከጥላቻ እናጸዳለን” የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሕዳር 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ከተማችንን ከቆሻሻ፣ ሃገራችንን ከጁንታ፣ ከከሀዲነትና ከጥላቻ እናጸዳለን” በሚል መሪ ቃል በሁሉም አካባቢ የጽዳት ዘመቻ ተካሄደ፡፡
በጽዳት ዘመቻው ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ የከተማዋ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ምክትል ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት እኛም ጽዳትን ባህላችን አድርገን የዘመቻ ቀን ሳንጠብቅ ሁልጊዜ እራሳችንን እና ከተማችንን ከሚታይ እና ከማይታየው ቆሻሻ እና ክፉ አስተሳሰብ እናጽዳ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ምክትል ከንቲባዋ በጽዳት ዘመቻው እንደገለጹት አዲስ አበባ ከተማን ከብዙ ቆሻሻዎች በተለይ ከህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች ተግባራት በማጽዳት ለኑሮ ምቹ እና የጎብኚዎች መዳረሻ እንድትሆን ሁሉም መረባረብ ይኖርበታል ብለዋል።
የጽዳት ዘመቻው በሁሉም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ተካሄዷል፡፡