Fana: At a Speed of Life!

ሕግ የማስከበር ስራውን በማፋጠን ጁንታው ሊያደርስ ያሰባቸውን ተጨማሪ ጥፋቶች ማስቀረት ተችሏል- ብርጋዴር ጄነራል ብርሃኑ ጥላሁን

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)ሕግ የማስከበር ስራውን በፍጥነት በማከናወን ጁንታው ሊያደርስ ያሰባቸውን ተጨማሪ ጥፋቶች ማስቀረት መቻሉን የምዕራብ ዕዝ የሎጂስቲክስ ክፍል ምክትል አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ብርሃኑ ጥላሁን ተናገሩ።

ብርጋዴር ጄነራል ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሕወሓት ጁንታን ጥቃት ተከትሎ የሃገር መከላከያ ኃይሉ ፈጣንና ውጤታማ የህግ ማስከበር ዘመቻ እያካሄደ ይገኛል።

ቡድኑ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ክህደት በፈጸመበት ወቅት የቻለውን ያህል ወታደራዊ ቁሶችን ከዘረፈ በኋላ ያልቻለውን ደግሞ አበላሽቶ ሄዷል ብለዋል።

“የትግራይ ህዝብ በዚህ ቡድን እኩይ ተግባር ማዘኑን በየደረስንባቸው አካባቢዎች መረዳት ችለናል” ነው ያሉት።

የሕወሓት ጁንታ በትግራይ የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማውደም የህዝብ ጠላት መሆኑን በግልጽ ማሳየቱን ጠቅሰው፤ “በዚህ ድርጊቱ በርካታ የአካባቢው ነዋሪ ማዘናኑን ገልጾልናል” ብለዋል።

የሕወሓት ፅንፈኛ ቡድን የተለያዩ የሃሰት ወሬዎችን በማሰራጨት ነዋሪዎች ከየአካባቢያቸው እንዲለቁ ማድረጉንም አስታውሰዋል።

“ይህንን ያደረገበት ዋናው ምክንያትም ለዘረፋ እንዲመቸው መሆኑ ተደርሶበታል” ብለዋል ብርጋዴር ጀነራል ብርሃኑ።

እንደ ብርጋዴር ጄነራል ብርሃኑ ገለፃ፤ የህወሓት ጁንታ የቡድኑን ታጣቂዎች የሲቪል ልብስ በማልበስ የሃገር መከላከያ ሰራዊቱን እንዲወጉ ለማድረግ ጥረት አድርጓል።

ሆኖም ሰራዊቱ የህግ ማስከበር ዘመቻውን በጥንቃቄና በውጤታማነት ለማከናወን እንደተቻለ ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.